የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን የትግበራ ሂደት የሚያቀናጅና የሚከታተል የሽግግር ፍትሕ ቋሚ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር ይሰየማል- ፍትሕ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን የትግበራ ሂደት የሚያቀናጅና የሚከታተል የሽግግር ፍትሕ ቋሚ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር ይሰየማል- ፍትሕ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016 (ኢዜአ)፦ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን የትግበራ ሂደት የሚያቀናጅ፣ የሚከታተልና ሂደቱን እየገመገመ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የሽግግር ፍትሕ ቋሚ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር የሚሰየም መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የድርጊት መርሃ-ግብር/ ፍኖተ- ካርታ/ ረቂቅ ሰነድ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት እየተደረገ ነው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ መሠረት ያደረገ፣ የተቀናጀ የሽግግር ፍትሕ ሂደት መምራትና ገቢራዊ የሚደረግበት ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወቃል፡፡
ፖሊሲው የወንጀል ምርመራና ክስ፣ እውነትን መፈለግ፣ ዕርቅ፣ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ምህረት እና ማካካሻ እንዲሁም ለገቢራዊነቱ ገንቢ የሕግ፣ የአሠራር እና የአደረጃጀት አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ያለመ ነው።
የተለያዩ ስልቶች ተፈጻሚ የሚሆኑበትን የጊዜ ወሰን ማሳየት፤ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን ሚና፣ በትግበራ ሂደቱ ክልሎች እንዲሁም ልዩ ትኩረትን የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ተጎጂዎችን ተሳትፎና አበርክቶ የሚያመላክት ነው።
የሽግግር ፖሊሲውን መተግበር የሚያስችሉ ተቋማትን ለማቋቋም የሚያስፈልጉ የሥነ-ሥርዓት እና ፍሬ ነገር ሕጎች እየተዘጋጁ መሆኑም ይታወቃል።
ከዚህም ባለፈ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የድርጊት መርሃ-ግብር /ፍኖተ- ካርታ/ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ እንዳሉት፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው የሚፈለገውን ፍትሕ የማስፈን ግብ እንዲያመጣ በነፃና ገለልተኛ ባለሙያዎች መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚዘጋጁ ሰነዶችና የሚወጡ ሕጎችም በገለልተኛ አካል እንዲዘጋጁ የሚደረግ መሆኑን ነው የገለጹት።
ለዚህም ፖሊሲው ላይ የተመላከቱ ተቋማት በሕግ ተቋቁመው ኃላፊነታቸውን እስከሚረከቡ ድረስ የሚከናወኑ ተግባራትን በጊዜያዊነት የሚያስተባብር "የሽግግር ፍትሕ ጊዜያዊ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር መድረክ" ይሆናል ብለዋል።
በፖሊሲው የተመላከቱ ተቋማት ከተቋቋሙ በኋላም የትግበራ ሂደቱን አፈጻጸም የሚያቀናጅ፣ የሚከታተልና ሂደቱን እየገመገመ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ እንዲሁም በአተገባበር ወቅት የሚነሱ ልዩነቶችን የሚፈታ 14 ከፍተኛ አመራሮችን የያዘ "የሽግግር ፍትሕ ቋሚ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር" ይሰየማል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የቀድሞ የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር እና ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚካተቱበት ይሆናልም ነው የተባለው።