ኢትዮጵያ ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ትግበራ መርሃ-ግብርን ይፋ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ትግበራ መርሃ-ግብርን ይፋ አደረገች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ትግበራ መርሃ-ግብርን ይፋ አደረገች።
በይፋ ማድረጊያ መርሃ-ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮች፣ የፌዴራልና የክልል ተቋማት አመራሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለተከታታይ ድርቅና የጎርፍ አደጋ መጋለጧን አንስተዋል።
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም ተግባራዊ ምላሽ ያስፈልጋል በሚል አቋም ፖሊሲዎች ነድፋ እየተገበረች ነው ብለዋል።
ለዚህም በፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መሠረት እስከ 2022 ዓ.ም የሚቆይ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የአየር ንብረት ለውጥ የምላሽ ዕቅድ አዘጋጅታለች ብለዋል።
ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረገ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እንዳላትም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ሚናዋን በተግባር ካሳየችባቸው ሥራዎች መካከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በአምስት ዓመታት ከ32 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም ጥረትና ትጋቷን ማሳየቷን ገልፀዋል።
ስድስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም መጀመሩን ገልጸው፤ ለስኬቱ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የበጋ ስንዴ የልማት መርሃ-ግብርም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ቁርጠኝነትን ያሳየ ሀገራዊ የልማት ኢኒሼቲቭ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በታዳሽ ኃይል ልማት የተጀመሩ ሥራዎች የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ግባችንን የሚያሳካ ስለመሆኑ አንስተው መንግሥት የአየር ንብር ለውጥ ተፅዕኖ ቅነሳ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያመጣው ተፅዕኖ አኳያ ዛሬ ይፋ የሚሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ማስተግበሪያ መርሃ-ግብር ውጤት እንዲያመጣ የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሚና ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሏትን በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣትም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሀገራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅዷን በማሻሻል ለተ.መ.ድ. የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት ከሁለት ዓመት በፊት ማስገባቷን አስታውሰዋል።
ለዕቅዱም የትግበራ መርሃ-ግብር ማዘጋጀቷን ጠቁመዋል።
በተሻሻለው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ትግበራ ዕቅድ፤ ኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በ68 ነጥብ 8 በመቶ የመቀነስ ግብ ማስቀመጧን ገልፀዋል።
የትግበራ መርሃ-ግብሩ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚናን በተቀናጀ መልኩ የመወጣት ቁርጠኝነትን የሚያሳይና ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ያላትን ተምሳሌታዊ እርምጃ የሚያሳይ ነው ብለዋል።