የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ሞተራይዝድ ሻለቃ የትኛውንም ግዳጅ በላቀ ብቃት ለመፈጸም ዝግጁ ነው- የሻለቃው ከፍተኛ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ሞተራይዝድ ሻለቃ የትኛውንም ግዳጅ በላቀ ብቃት ለመፈጸም ዝግጁ ነው- የሻለቃው ከፍተኛ አመራሮች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ሞተራይዝድ ሻለቃ በቀጣናው በየትኛውም ጊዜና ቦታ የሚሰጠውን ግዳጅ በላቀ ብቃት ለመፈጸም የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያለው መሆኑን የሻለቃው ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አገራትን በአባልነት ያቀፈው የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ለቀጣናው የሰላምና ደህንነት ፈጣን ምላሽ የመስጠት ዓላማ ይዞ በፈረንጆቹ 2004 ነበር የተመሰረተው።
በአባል ሀገራቱ ስምምነት መሰረት ሀገራቱ ለተጠንቀቅ ኃይሉ በሰው ኃይልና በሎጅስቲክስ የተሟላ ሰራዊት ማዋጣት የሚጠበቅ ሲሆን ኢትዮጵያም ለዚህ ተልዕኮ የራሷን ሞተራይዝድ ሻለቃ አደራጅታለች።
የኢትዮጵያ ሞተራይዝድ ሻለቃም በተጠንቀቅ ኃይሉ ልዑክ ተጎብኝቶ የዝግጁነት ማረጋገጫ ግምገማ ተደርጎለት፣ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት በተሟላ ቁመና ላይ መሆኑ ተረጋግጧል።
በመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር የዓለም አቀፍና ጎረቤት ሀገራት ጉዳዮች ዳሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል ሰብስቤ ዱባ፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መጠበቅ በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም በምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኅይል ለማዋጣት የገባችውን ቃል በማክበርና ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለተጠንቀቅ ኅይሉ ሞተራይዝድ ሻለቃ አደራጅታ ለግዳጅ ዝግጁ ማድረጓን ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተደራጀው ሻለቃ በቀጣናው በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ የሚሰጠውን ግዳጅ በላቀ ብቃትና ፍጥነት ለመፈጸም ሁለንተናዊ ዝግጁነት አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሞተራይዝድ ሻለቃ ዝግጁነት የጎበኘው የተጠንቀቅ ኃይሉ ልዑክ የሞተራይዝድ ሻለቃን ሁሉን አቀፍ ዝግጁነት በማረጋገጥ አድናቆት ችረዋል።
በአፍሪካም ሆነ በዓለም ሰላምና ጸጥታ ማስጠበቅ ተልዕኮዎች የኢትዮጵያ የላቀ ሚና እና ጠንካራ ተሳትፎ መኖሩን ጠቅሰው ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ሞተራይዝድ ሻለቃ ሎጀስቲክስ ኮሎኔል እንዳለ ዴንሳ፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በየሀገራቱ ሰላም በማስከበር የነበራትን አኩሪ ገደል ማስቀጠሏን ጠቅሰዋል።
አሁንም ለቀጣናው ሀገራት ሰላም ማስከበር ያደራጀችው ሻለቃ በሁሉም ረገድ ብቃትና ዝግጁነት ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከሞተራይዝድ ሻለቃ መኮንኖች መካከል መቶ አለቃ እድሉ ዮሐንስና መቶ አለቃ እታገኝ ሙላቱ፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት በተሰማራበት የተኛውም ግዳጅ በሥነ ምግባሩና በግዳጅ አፈጻጸሙ ከፍ ያለ ስም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሻለቃዋ አመራርና አባላትም በየትኛውም ግዳጅ በጥብቅ በላቀ ብቃት ለመፈጸም ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
ከተጠንቀቅ ኃይሉ ሻለቃ የፖሊስ አመራሮች መካከል ኮማንደር መሰለ ካሳና ዋና ኢንስፔክተር ገነት በላይሁን፤ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ግዳጅ መፈጸም የሚያስችል በቂ ስልጠና እና ዘግጁነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።