ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀምራል

 አዲስ አበባ 26/2016የ2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ እና የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።

ውድድሩ ዛሬ ቀጥሎ ሲውል ሃዋሳ ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 7 ሰዓት በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 2 ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ቡድኑ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 12 ግቦችን አስተናግዷል። በዚህም 38 ነጥብ በመያዝ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 1 ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ 1 ጊዜ ተሸንፏል። 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።በ5ቱ ጨዋታዎች 2 ግብ ሲያስቆጥር 6 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በ34 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ30ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ሀድያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ጨዋታዎች 1 ጊዜ ድል ሲቀናው 3 ጊዜ ተሸንፏል። 1 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች 6 ግቦችን ሲያስቆጥር 7 ጎሎችን አስተናግዷል።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ሀድያ ሆሳዕና በ38 ነጥብ ተመሳሳይ ነጥብ ያለውን ሃዋሳ ከተማን በግብ ክፍያ በልጦ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት 5 የሊጉ ጨዋታዎች 4ቱን ሲያሸንፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል። ቡናማዎቹ  በ5ቱ ጨዋታዎች 15 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፉ 4 ጎሎችን አስተናግደዋል።

በነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በ51 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው አይዘነጋም።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርኃ ግብር የመክፈቻ ጨዋታዎች ላይ የመጫወቻ ሜዳና የሰዓት ለውጥ መደረጉ መገለጹ የሚታወስ ነው።

በ30ኛ ሳምንት ሃዋሳ ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 9 ሰዓት እንዲሁም ሀድያ ሆሳዕና ከኢትዮዮጵያ ቡና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ መርኃ ግብር ወጥቶላቸው ነበር።

የመክፈቻ ጨዋታዎቹ የቀጥታ ሽፋን እንደማይኖራቸውና በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ሊካሄዱ የነበሩት ጨዋታዎች በአስገዳጅ ምክንያት ወደ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ መቀየራቸውን የፕሪሚየር ሊጉ ውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ገልጿል።

የሊጉ የ30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 9 ሰዓት፣ ሲዳማ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ61 ነጥብ እየመራ ይገኛል። መቻል በ60 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዞ ይከተላል።

የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ የግብ አስቆጣሪነትን ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌማን በ18 ግቦች እየመራ ነው።

የመቻል አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ በ14 እንዲሁም የአዳማ ከተማው የፊት መስመር ተሰላፊ ዮሴፍ ታረቀኝ በ12 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም