በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችን ከቀጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ የስራ አውደ ርዕይ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችን ከቀጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ የስራ አውደ ርዕይ ተካሄደ
ሀዋሳ፤ ሰኔ 25 / 2016 (ኢዜአ)፡- በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ከተለያዩ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል የስራ አውደ ርዕይ ተካሄደ፡፡
በስራ አውደ ርዕዩ ላይ ቀጣሪ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ተመራቂ ተማሪዎች የስራ ማመልከቻቸውን በማስገባትና ራሳቸውን በማስተዋወቅ ትስስር ፈጥረዋል።
በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢንጂነር ፍስሃ ጌታቸው ፤ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ዓመታት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ100 ሺህ በላይ ምሩቃንን ለስራ ገበያ ማቅረቡን አውስተዋል።
የትምህርት አዳዲስ ፕሮግራሞችን ከመክፈት ይልቅ የተከፈቱትን የጥራት ደረጃ ማሳደግና ፕሮግራሞቹ ከገበያው ፍላጎት ጋር እንዲመሳሰሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተመረጡ ፕሮግራሞች ላይ በማተኮር የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተው፤ የተጀመረው የለውጥ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ከቀጣሪ ድርጅቶችና ኢንደስትሪዎች ጋር የሚደረገው ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የመምህራን አቅም ማጎልበትና አግባብነት ያላቸውን የትምህርት ፕሮግራሞች መስጠት እንዲሁም የምሩቃኑን የመቀጠር ምጣኔ ማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለዚህ የሚያግዝ አውደርዕይ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ዛሬ ከ"ኢንፎማይንድ ሶሊዩሽን ደረጃ ዶት ኮም ፕሮግራም " ጋር በመተበባር የተዘጋጀው የስራ አውደ ርዕይም ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን የለውጥ ስራ የሚያግዝና ከ5 ሺህ በላይ የዘንድሮ ተመራቂዎችን ከቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሙያና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ክብረት ፈቃዱ በበኩላቸው ፤ የተማረ የሰው ሃይልን የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል በክህሎት ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ላለፈው አንድ ዓመት የዘንድሮ ተመራቂዎች የክህሎት ስልጠናዎች በማዘጋጀት ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚገናኙበትን እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
ዛሬ በዩኒቨርሲቲው የተከፈተው የስራ አውደ ርዕይ ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ ከ70 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች የተገኙበትና ለዘንድሮ ተመራቂዎች የስራ እድል የሚፈጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
26 ከሚደርሱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተመራቂ ተማሪዎች ላይ እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በ"ኢንፎማይንድ ሶሊዩሽን የኢትዮ ጆብስና ደረጃ ዶትኮም "ስራ አስኪያጅ አቶ የሱፍ ረጃ ናቸው።
በዚህም በየዓመቱ የስራ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ተመራቂዎችን ከቀጣሪዎች ጋር ለማገናኘት በተጀመሩ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በየዓመቱ በተለያዩ ዩኒቨርሲተዎች በሚደረጉ ተመራቂዎችን ከቀጣሪዎች የማገናኘት መድረክ ለሚቆጠሩ ተማሪዎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
ሌላው ቀጣሪ ድርጅት በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የሰው ሃብት አስተዳደር ወይዘሪት ፍሬህይወት አሳምነው በበኩሏ፤ የስራ አውደ ርዕዩ ቀጣሪዎች የሚፈልጉትን በመስኩ የሰለጠነ ባለሙያ ለማግኘት የሚያስችላቸው መድረክ እንደሆነ ገልጻለች።
በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተዘጋጀ ተመሳሳይ መድረክ በርካታ ተመራቂ ተማሪዎችን መቅጠራቸውን ገልጻ የተጀመረው ስራ ቀጣሪዎችንም ሆነ ተመራቂዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብላለች።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ"ኢኳቲክ ሳይንስና ፊቸሪ " ተመራቂዋ በእምነት በየነ በበኩሏ፤ በመጨረሻው ዓመት በተለያዩ መስኮች ክህሎቷን የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን ማግኘቷን ገልጻ ፤ በዛሬ የስራ አውደ ርዕይ ያላትን እውቀት ለቀጣሪ ድርጅቶች በመሸጥ ከበርካታ ድርጅቶች ጋር መተዋወቋን ተናግራለች።
በስራ አውደ ርዕዩ ላይ ከ70 የሚበልጡ ቀጣሪ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን ተመራቂ ተማሪዎች የስራ ማመልከቻቸውን በማስገባትና ራሳቸውን በማስተዋወቅ ትስስር ፈጥረዋል።