የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ጠንካራ አገርን የመገንባት ተልዕኮን የያዘ ነው -ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ጠንካራ አገርን የመገንባት ተልዕኮን የያዘ ነው -ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር)
መቀለ ፤ ሰኔ 25/2016ዓም (ኢዜአ)፦ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ጠንካራ አገር የመገንባት ተልዕኮ እንዳለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ቀንአ ያደታ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት በክልሉ ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና እድሳት የሚውል በተጠሪ ተቋማቱ የተሰበሰበ የ23 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህነት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ቀንአ ያደታ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የ2016 ዓ/ም የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተግባራዊ አየተደረገ ነው፡፡
በዚህም የዜጎች ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክሩ፣ አቅመ ደካሞችን የማገዝ፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን የማጠናከር፣ ጽዱ ኢትዮጵያን የመፍጠር እና የጎርፍ አደጋን የመከላከል ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጊዜያዊ እና አንገብጋቢ ችግሮችን ከመፍታት በዘለለ በሂደት ጠንካራ አገርን የመገንባት ተልዕኮን የያዘ ነው ብለዋል፡፡
ጠንካራ አገርን በመገንባቱ ሂደት የወጣቱ ትውልድ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትግበራን በአግባቡ መፈጸም እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት በክልሉ ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና እድሳት የሚውል በጽሕፈት ቤቱ ተጠሪ ተቋማት የተሰበሰበ 23 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
በትግራይ ክልል በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጽዱ ኢትዮጵያ አካል የሆነው የከተሞች እና የአካባቢ ጽዳት ስራ ተግባራዊ እንደሚደረግም አመልክተዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለተደረገው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት "በራስ አቅም እና በራስ ተነሳሽነት ከተሰራ ችግሮቻችን በእኛ አቅም እንደሚፈቱ ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡
በክልሉ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሁሉም ወረዳዎች እንደተጀመረ እና አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚሳተፉም በጊዜያዊ አስተዳደሩ የወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሽ ስዋጋድስ ተናግረዋል።