ቀጥታ፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ ሰው ተኮር የልማ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

ሀዋሳ ፤ ሰኔ 25/2016 (ኢዜአ)፦ በጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተጀመሩ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት አመራር አባላት ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት በተያዘው የክረምት ወቅት በሲዳማ ክልል የሚያካሂዱትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ አስጀምረዋል።

የጽህፈት ቤቱና የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በክልሉ አለታ ጩኮ ከተማ ማንጉዶ ቀበሌ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና የችግኝ ተከላን አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሃመድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሲዳማ ክልል ለ22 አቅመ ደካሞች የቤት ግንባታን ጨምሮ ሌሎች ሰው ተኮር ተግባራት እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።

ቤቶቹ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በሁለት ወራት ውስጥ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ገልጸዋል።


 

የሲቨል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ስመኝ ውቤ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ከማገዝ ባለፈ የሕዝቦችን ትስስር ከማጠናከር አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም የበጎ ፈቃድ ተግባራት በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል ገልጸው፤''ለዚህም እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ሃላፊነታችንን እንወጣለን'' ብለዋል። 


 

ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ሰዎችን ከችግር ያወጣ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ናቸው።


 

የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው፤ በክልሉ እየተካሄደ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ሰዎችን እየጠቀመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፈው ክረምት ከ1 ሺህ 300 በላይ ቤቶች መገንባትና ማደስ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ ዘንድሮም ሁለት ሺህ የመኖሪያ ቤት ዕድሳትና ግንባታን ጨምሮ በ13 የተለዩ ተግባራት  እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

የቤት ዕድሳት የሚደረግላቸው በአለታ ጩኮ ከተማ የማንጉዶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዘላለም ኦርማቶ፣ በአሁኑ ወቅት የጤና እክል እንዳለባቸው ገልጸው፤ ቤታቸው ያረጀ በመሆኑ በዝናብና ውርጭ ሳቢያ ችግር ሲደርስባቸው መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ቤታቸውን በበጎ ፈቃድ ለሚያድሱላችው አካላትም ምስጋና አቅርበዋል። 

ሌላኛዋ ቤት የሚታደስላቸው መሰረት ዋኖሌ በበኩላቸው፤ ባለቤታቸው በመሞቱ ምክንያት በችግር ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን እንደሚያሳድጉ ገልጸው፤ በድንገት መጥተው ቤታቸውን ለማደስ የጀመሩ አካላትን አመስግነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም