የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ስምንት ጉዳዮች መርምሮ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ስምንት ጉዳዮች መርምሮ አጸደቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፦የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን አሥራ ሁለት ጉዳዮች በመመርመር ስምንቱን አጸደቀ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ትናንትና ዛሬ አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ የአሰራር ሥርዓት ደንብ ላይ በመወያየት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
በመቀጠል ምክር ቤቱ የሕገ-መንግሥት ትርጉምና የውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚል ያቀረባቸውንና የሕገ-መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ያቀረባቸውን ጉዳዮች መርምሯል የውሳኔ ኃሳብ በማቅረብ አፀድቋል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ቋሚ ኮሚቴው የሕገ-መንግሥት ትርጉምና የውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚል ያቀረባቸውን አሥራ ሁለት ጉዳዮች በመመርመር ስምንቱን ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል፣አራቱን ጉዳዮች ደግሞ የሕገ-መንግሥት ትርጉም አይገባውም በማለት ለምክር ቤቱ የውሳኔ ኃሳብ መቅረቡን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱም የቀረቡለትን ጉዳዮች በመርመር የውሳኔ ኃሳብ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን ገልፀዋል።
በመቀጠል ቋሚ ኮሚቴው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ-መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል በተሰጣቸው ውሳኔዎች ቅር በመሰኘት ለምክር ቤቱ በይግባኝ የቀረቡ አንድ መቶ አስራ ሰባት ጉዳዮችን አስመልክቶ ቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ኃሳብ ለምክር ቤቱ መቅረቡን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱም በቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን የውሳኔ ኃሳብ ላይ ከተወያያ በኋላ አንድ መቶ አስራ አምስቱን ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም እንዲሁም ሁለት ጉዳዮች ደግሞ በቋሚ ኮሚቴው የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት በሙሉ ድምጽ በመቀበል ማዕደቁን የተናገሩት።
ምክር ቤቱ የሕገ-መንግሥት ትርጉምና ያስፈልጋቸዋልና አያስፈልጋቸውም በሚል ወሳኔ በተሰጠባቸው እንዲሁም ለምክር ቤቱ ይግባኝ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በትኩረት ይመለከታል ብለዋል።
በተለይም የሕ-መንግሥት ትርጉም መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወይንም ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ጉዳዮች የተሰጡ ውሳኔዎችን መሰረት በማድረግ ለጉዳዮቹ እልባት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ አባላትን በመተካት ምክር ቤቱ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን መደበኛ ጉባኤ ተጠናቋል።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 83 ሕገ-መንግሥትን ስለመተርጎም ንኡስ አንቀጽ 1 እና 2 የሕገ-መንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ በፌደሬሽኑ ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚያገኝና የፌደሬሽን ምክር ቤት፤ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ በሚያቀርብለት ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳይ ላይ በሰላሳ ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይደነግጋል።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 84 ንኡስ አንቀጽ (3.ሀ) ሥር እንደተደነገገው በአጣሪ ጉባኤው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ባለጉዳይ ቅሬታውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት በይግባኝ ማቅረብ እንደሚቻልም ተደንግጓል።