የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሰራዊት ግንባታና የተደራጀ የትጥቅ ዝግጅት ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ የላቀ ሚና አለው- የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሰራዊት ግንባታና የተደራጀ የትጥቅ ዝግጅት ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ የላቀ ሚና አለው- የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሰራዊት ግንባታና የተደራጀ የትጥቅ ዝግጅት በቀጣናው ሰላምና ጸጥታ የመሪነት ሚናዋን በአግባቡ እየተወጣች መሆኗን የሚያረጋግጥ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ገለጸ።
የአፍሪካ ህብረት በፈረንጆቹ 2002 በደቡብ አፍሪካ ደርባን ባደረገው የመጀመሪያ ይፋዊ ጉባኤ ላይ አፍሪካ በአምስት ክፍለ አህጉር የተደራጀ የተጠንቀቅ ኃይል እንዲኖራት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በ2004 በአዲስ አበባ ባደረገው ስብሰባ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል በቀጣናው ያሉ የጋራ የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን ለማጠናከር ተመስርቷል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 አባል ሀገራት ያሉት የተጠንቀቅ ኃይሉ በወታደራዊ፣ በፖሊስና በሲቪል የሰው ኃይል የተዋቀረ ሲሆን ዋና ተልዕኮውም በቀጣናው ለሚከሰቱ የፀጥታ ስጋቶች ፈጣን ምላሽ መስጠት ነው።
ለዚህ ኃይል አባል ሀገራት በሰው ኃይልና በሎጅስቲክስ የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን ኢትዮጵያም ራሱን የቻለ ሞተራይዝድ ሻለቃ ከመመደብ ጀምሮ በቂ ዝግጅት ማድረጓን አሳይታለች።
በምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ፤ የተመራ የዝግጁነት አረጋጋጭ ልዑክ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ያዘጋጀችውን ሞተራይዝድ ሻለቃ ጦር ሰፈር ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ልዑኩ ኢትዮጵያ ቃል በገባችው መሰረት ለተጠንቀቅ ኃይሉ ያደረገችውን የሰራዊትና የሎጅስቲክስ ቁመናም በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶች መሰረት የማረጋገጥ ስራ አከናውኗል።
የተጠንቀቅ ኃይሉ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል ፖል፤ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ኃይል ዘመናዊና በትጥቅም ሆነ በሰው ኃይሉ የተሟላና አስተማማኝ ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዝግጁነት በተቀመጠው መስፈርት መሰረት በከፍተኛ ደረጃ የሚሰጠውና ለቀጣናው ሰላምና ፀጥታ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑንም ገልጸዋል።
የዝግጁነት ገምጋሚ ቡድኑ በሌሎች አባል ሀገራትም ተገኝቶ ምልከታ እንደሚያደርግ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የሚደነቅና ተምሳሌታዊ ተሞክሮ ያላት ስለመሆኗ አብራርተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠናቀቅ ኃይል የኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ጌታቸው አሊ፤ አባል ሀገራት ለተጠንቀቅ ኃይሉ የሚያዋጡትን ዝግጁነት የመስክ ምልከታና ግምገማ መጀመሩን ገልጸዋል።
የገምጋሚ ቡድኑ መመዘኛዎች ከዓለም አቀፍና ከአፍሪካ ሕብረት መስፈርቶች ጋር የተጣጣሙ ናቸው ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በተግባራዊ ፍተሻና የዝግጁነት ማረጋገጫ ምዘና መስፈርት መሰረት የተዘጋጀና የተደራጀ ኃይል እንዳላት ቡድኑ አረጋግጧል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ የካበተ ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን ያነሱት ብርጋዴር ጄነራሉ፤ የአሁኑ ዝግጁነቷም በቁርጠኝነቷ መቀጠሏል የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኮሞሮስና ሲሸልስን በአባልነት የያዘና በቀጣናው ለሚነሱ የፀጥታና የደህንነት ስጋቶች ፈጣን ምላሽ መስጠትን ዓላማ ያደረገ ነው።