ቀጥታ፡

የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች የሥራ ላይ ደኅንነት መመሪያዎችን በአግባቡ ሊተገብሩ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፦ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች የሥራ ላይ ደኅንነት መመሪያዎችን በአግባቡ በመተግበር የአደጋ ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እንደሚጠበቅባቸው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ጋር በመተባበር በአምስት ዙር የተሰጠውን የኮንስትራክሽን ሙያ ላይ የደኅንነት ሥልጠና ላጠናቀቁ ባለሙያዎች የእውቅና ሰርቲፊኬት ሰጥቷል፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ይገኛል፡፡

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ ከሚያስችሉ ሁኔታዎች ውስጥ የሥራ ላይ ደኅንነትን ማስጠበቅ አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ ዘርፉ በርካታ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ የሥራ ላይ ደኅንነት መመሪያዎችን በተገቢው መልኩ በመተግበር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ ይገባል ነው ያሉት፡፡


 

የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች የደኅንነት ግብዓት ከማሟላት ባሻገር ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ማከናወን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማሪያም፤ በዘርፉ ለተሰማሩ 194 ባለሙያዎች በአምስት ዙር የሙያ ላይ ደኅንነት ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናውም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን የአደጋ ተጋላጭነት መቀነስን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ፤ ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትን አቅም ማጎልበት ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሥልጠናውም ይህን ታሳቢ በማድረግ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ሰልጣኞች ወደ ሥራ ሲሰማሩ ተገቢውን የደኅንነት መመሪያ በመከተል አደጋን በመቀነስ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም