ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ማውጣት ላይ ትኩረት ማድረጉን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ማውጣት ላይ ትኩረት ማድረጉን ገለጸ
ጅማ/ ነቀምቴ፣ ሰኔ 25/2016 (ኢዜአ) የመማር ማስተማር ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ማውጣት ላይ ትኩረት ማድረጉን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 1ሺ 747 ተማሪዎችን በመጀመርያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ዛሬ አስመርቋል።
በመጀመሪያ ዲግሪ 1ሺ 471፣ በሁለተኛ ዲግሪ 276 እና በሶስተኛ ዲግሪ ደግሞ 20 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራት የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።
በተለይም የህብረተሰቡን ችግር መፍታት የሚችሉ የምርምር ስራዎችም በተለያዩ መስኮች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ማውጣት ላይ ትኩረት ማድረጉንም ገልጸዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰው ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘነብወርቅ ገብረ ጻዲቅ በበኩላቸው ተመራቂዎች በተማሩት ሙያ ስራ በመፍጠር ሀገርና ህዝባቸውን ለመጥቀም መስራት አለባቸው ብለዋል።
ወጣት ተመራቂዎች ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸው ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው በተሰማሩበት ሁሉ ለውጤታማነት መትጋት እንዳለባቸውም መክረዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ለዓመታት የደከሙበት የትምህርት ጉዞ ፍሬ በማፍራቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ሮቤል ውሂብ፣ ''በተመረቅኩበት ሙያ ተሰማርቼ ሀገሬን እና ወገኔን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ በዚህም ደስተኛ ነኝ'' ብሏል።
''ትምህርቴን ጨርሼ የግል ቢዝነስ ለመክፈት አቅጃለሁ'' ያለችው ደግሞ የኢኮኖሚክስ ተመራቂዋ ራሄል አየለ ናት።
በተመሳሳይ የወለጋ ዩኒቨርስቲ ሲያስተምር የቆየውን 2 ሺህ 236 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ፣ ተመራቂዎች ከብዙ ውጣ ውርድ በኋላ ለዚህ በመብቃታቸው ''እንኳን ደስ አላችሁ'' ብለዋቸዋል።
ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲው በቀሰሙት እውቀት ሀገራችውን እና ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
ዮኒቨርስቲው ላለፉት 19 አመታት የአካባቢውን ማህበረሰብ በተለያየ መልኩ ሲያግዝ መቆየቱን ገልጸው በቀጣይም ይህንኑ ተግባር እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።
ተመራቂዎቹ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።