የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ይኖራል-ኢንስቲቲዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ይኖራል-ኢንስቲቲዩቱ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ጠቆመ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ ይበልጥ እንደሚጠናከር አስታውቋል።
ስለሆነም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ስፍራዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ 30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ ዝናብ እንደሚኖር ጠቁሟል፡፡
በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአዲስ አበባ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በትግራይ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በሲዳማ ክልሎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ አመላክቷል፡፡
ዝናብ ሰጪ የሜትሮሎጂ ገጽታ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ እና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋ እና የተጠናከረ የደመና ክምችት እንደሚኖር ጠቅሷል፡፡
በዚህም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎችን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡
በዚሁ ወቅት የሚኖረው ርጥበት የመኸር ሰብሎችን ለመዝራት እና ማሳን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የሚጠበቀው ርጥበት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት በምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ አካባቢ ለሚገኙ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለአረንጓዴ ልምላሜ ፣ ለግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል፡፡
እንዲሁም በአፋር ደናክል ፣ በታችኛው አዋሽ፣ በመካከለኛው ገናሌ ዳዋ የግድቦችን የውሃ መጠን በማሻሻል አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው አመላክቷል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የሐምሌ ወር ዝናብ ከሚኖረው አወንታዊ ጠቀሜታ ባሻገር በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ሊጥል ስለሚችል ህብረተሰቡ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡