ቀጥታ፡

በባሌ አካባቢ የሚከናወነውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በሳይንሳዊ ምርምር እንደሚያግዝ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ

ሮቤ፤ ሰኔ 24/2016(ኢዜአ)፦መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በባሌ አካባቢ የሚከናወነው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን በሳይንሳዊ ምርምር እንደሚያግዝ ገለጸ። 

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የጎባ ቅርንጫፍ ጋር በመቀናጀት  "የምትተክል ሀገር፣ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዛሬ አካሄደዋል። 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬት በየጊዜው ከሚያደርገው ተሳትፎ በተጓዳኝ የችግኝ ተከላው በሳይንሳዊ ምርምር ያግዛል። 

የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በብዝሃ ህይወት እና በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ እያካሄዱ የሚገኙት ምርምሮች የዚሁ ጥረት ማሳያ እንደሆኑ አመልክተዋል። 

በዩኒቨርሲቲው በመካሄድ ላይ የሚገኙት ምርምሮችና የችግኝ ተከላ ሥራው በአየር ንብረትና በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ችግሮችን በጥናት በመለየት ምላሽ ለመስጠት የጎላ ድርሻ እንዳላቸውም አመልክተዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ሥራውም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንዲያስችልና ለኢኮኖሚ እድገት መፍትሄ በሚሆን አግባብ መከናወን እንዳለበት አመላክተዋል። 

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ ዛሬ የተካሄደውን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በአብነት አንስተዋል። 


 

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይም የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ በመደረጋቸው ጠፍተው የነበሩ የዱር እንስሳትና ምንጮች እየጎለበቱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል። 

በችግኝ ተከላው ላይ ከተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት መካከል መምህር አብዱልፋታህ አብዱ፣ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ እንደ ዜጋ በየጊዜው ከመሳተፍ በሻገር ለስኬታማነቱ በምርምር የማገዝ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

መርሐ ግብሩ የተራቆቱ መሬቶችን አረንጓዴ ለማልበስ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሀገር በቀል የዛፍ ችግኝ ያካተተ በመሆኑ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በዘላቂነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የመርሐ ግብሩ ተሳታፊ አቶ ጥለሁን ገመቹ ናቸው። 

በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በጎባ ክፍለ ከተማ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የደን፣ የአትክልት፣ የእንስሳት መኖና ሌሎች ችግኞች መተከላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም