በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የክረምት ወቅት መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የክረምት ወቅት መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ተመለከተ
ጋምቤላ፣ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፡-በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የክረምት ወቅት መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የጋምቤላ ክልል ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል በመጪው የክረምት ወቅታዊ የአየር ትንበያ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በጋምቤላ መክሯል።
የማዕከሉ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በክልሉ በመጪው ክረምት መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ወቅታዊ የትንበያ መረጃ ያመለክታል።
በዚሁ የክረምት ወራት በክልሉ የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለእርሻ ስራ እንዲሁም ለእጽዋት ተስማሚና ምቹ መሆኑን ተናግረዋል።
በአንፃሩ በክልሉ በሚኖረው ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት ለጎርፍ አደጋና ለወባ ወረርሸኝ የመጋለጥ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ተናግረዋል።
በተለይም ደጋማ አካባቢ ሊጥል የሚችለው ከመደበኛ ያለፈ ዝናብ ባሮን ጨምሮ ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በመሆኑም በወንዞች አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መሪ ስራ አስፈፃሚው መክረዋል።
እንዲሁም ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ለወባ ትንኝ ምቹ የመራቢያ ጊዜን ስለሚፈጥር ወባን በመከላከል ረገድም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
የዕለቱ የምክክር መድረክ ዓላማ በክርምቱ የአየር ትንበያ መረጃ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የትብብር ስራን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ነው አቶ ተስፋሁን የተናገሩት።
የክልሉ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብርት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጄት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የመጪው የክረምት አየር ትንበያን መረጃ በአግባቡ በመረዳት ለግብርና ስራ የሚኖሩ እድሎችን መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም ከሚኖረው ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋና የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል ከወዲሁ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል አቶ ሙሴ።
በምክክር መድረኩ ላይ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት፣ የአመራር አባላትና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።