የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የኢትዮጵያ ሞተራይዝድ ሻለቃ በሰው ኃይልና በትጥቅ አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጡን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የኢትዮጵያ ሞተራይዝድ ሻለቃ በሰው ኃይልና በትጥቅ አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጡን አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የኢትዮጵያ ሞተራይዝድ ሻለቃ በሰው ኃይልና በትጥቅ አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጡን አስታወቀ።
በምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ፖል ካሁሪያ ጀማ የተመራ የዝግጁነት አረጋጋጭ ልዑክ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ያዘጋጀችውን ሞተራይዝድ ሻለቃ ጦር ሰፈር ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ኃይል በትጥቅም ሆነ በሰው ኃይሉ የተሟላ እንዲሁም በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ለግዳጅ ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዝግጁነት ለቀጣናው ሰላምና ፀጥታ ያላትን ነባር ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑንም ገልጸዋል።
የዝግጁነት ገምጋሚ ቡድኑ በሌሎች አባል ሀገራትም ተገኝቶ ምልከታ እንደሚያደርግ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ተምሳሌታዊ ተምክሮ ያላት ሀገር ሰለመሆኗ አብራርተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው አሊ በበኩላቸው የገምጋሚ ቡድኑ መመዘኛዎች ከዓለም አቀፍ እና ከአፍሪካ ሕብረት መስፈርቶች ጋር የተጣጣሙ ናቸው ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በተግባራዊ ፍተሻና የዝግጁነት ማረጋገጫ ምዘና መስፈርት መሰረት የተዘጋጀና የተደራጀ ኃይል እንዳላት ቡድኑ አረጋግጧል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ የካበተ ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን ያነሱት ብርጋዴር ጄነራሉ፥ የአሁን ዝግጅነቷም ይህ ቁርጠኝነት ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል።