የክልል መንግስታት ኅብረብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት የጋራ ትርክት ግንባታን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል- አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የክልል መንግስታት ኅብረብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት የጋራ ትርክት ግንባታን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል- አቶ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፦የክልል መንግስታት ኅብረብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት የጋራ ትርክት ግንባታን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ጊዜው የ1ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ-ጉባኤን በማጽደቅ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።
በጉባኤው የምክር ቤቱ አባላት የ2016 በጀት ዓመት የመንግስታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲ አንድነትና የሕገ-መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ እና የሕገ-መንግስትና የፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል የአፈፃጸም ሪፖርቶች ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።
በዚሁ ጊዜ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ የተዛቡና ነጠላ ትርክቶችን በማረቅ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ወንድማማችነት የሚያጠናክር የጋራ ትርክት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልል መንግስታትም በጋራ ጉዳዮች ላይ በመግባባት ችግሮች ሲያጋጥሙም በንግግርና በውይይት መፍትሔ የመስጠት ባህልን በማዳበር ለኢትዮጵያ ልዕልና በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ የክልል መንግስታትን በማጠናከር የጋራ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት የሚያስችሉ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት በቅንጅት የመስራት ባህል እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲ አንድነትና የሕገ-መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸኃፊ ባንቺይርጋ መለሰ፤ ተቋማዊ የመንግስታት ግንኙነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ፎረምና አደረጃጀቶች እየተፈጠሩ ነው ብለዋል።
በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የህዝቦችን ኅብረ ብሔራዊነት በማስጠበቅ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትስስርን፣ አንድነትና እኩልነት ማጎልበት የሚያስችሉ ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የመንግስታትን ግንኙነት ለማጠናከር በተከናወኑ የአስተምህሮ ተግባራት የሰላም ግንባታና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣጡን ተናግረዋል።
በቀጣይ የፌደሬሽን ምክርቤትና የክልል መንግስታትን ግንኙነት በማጠናከር አንድነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።