የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ለቅድመ መከላከል ስራዎች ከፍተኛ ትኩረት ተስጥቶ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ለቅድመ መከላከል ስራዎች ከፍተኛ ትኩረት ተስጥቶ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፦ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ ለቅድመ መከላከል ስራዎች ከፍተኛ ትኩረት ተስጥቶ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመካከለኛው አዋሽ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎችን አስጀምሯል።
የጎርፍ ቅድመ መካከል ስራውን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ በመገኘት አስጀምረዋል።
በመካከለኛው አዋሽ የሚከናወነው የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራ በክልሉ ገዋኔ፣ ገላእሎ፣ ዱለሳ እና አሩካ ወረዳዎች እንደሚከናወንም ተጠቁሟል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ፤ መንግስት የህብረተሰቡን የጎርፍ ተጋላጭነት በዘላቂነት ለመቀነስ ለቅድመ መከላከል ስራዎች ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።
የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎቹ በአጭር ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት የሚከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል የኃይድሮሊክ ስፔሻሊስት ፍጹም ከብዶ፤ በተጀመረው የሲቪል ስራ የወንዙን ግራና ቀኝ በመጥረግ የውሃ መሄጃ ቦታውን የማስፋት ስራ ይሰራል ብለዋል።
ይህም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ህብረተሰቡ የክረምቱን ወቅት ያለ ጎርፍ ስጋት እንዲያሳልፍ ያደረጋል ብለዋል።
የአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደን አብዱመሎ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በ25 ሺህ ሄክታር መሬት በለማ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
የጎርፍ አደጋው ቀበሌዎች ከወረዳ ማዕከላት ጋር እንዳይገናኙ እክል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ አሁን የተጀመረው ስራ የህብረተሰቡን ችግር በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የገዋኔ ወረዳ ነዋሪ ሰይድ ሀሰን በበኩሉ በአዋሽ ወንዝ ላይ የሚከናወነው የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ ለዘመናት ጥያቄያቸው ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ515 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የቅድመ ጎርፍ መከላከል የሲቪል ስራዎችን ለማከናወን ከአምስት ተቋራጭ ድርጅቶች ጋር ሰሞኑን የውል ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።