የኢትዮጵያና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቱርኪዬ መንግስት አመቻቺነት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡

የሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት በሁለቱ አገራት መካከል ላሉ አለመግባባቶች መፍትሄ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ግልፅና ወዳጅነት የተሞላበት የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት እንደነበር ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።


 

ሚኒስቴሩ በቱርኪዬ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን ጋባዥነት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በአንካራ ተገናኝተው መወያየታቸው ገልጿል።

በቱርኪዬ መንግስት አመቻቺነት የተካሄደው የሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት በሁለቱ አገራት መካከል ላሉ አለመግባባቶች መፍትሄ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ግልፅና ወዳጅነት የተሞላበት የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት እንደነበር በመግለጫው ተመላክቷል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የቱርኪዬ መንግስት ውይይቱን ለማመቻቸት ስለተጫወተው ገንቢ ሚናም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠልም መስማማታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች የቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ምክክሩን አገራቸው ለማስተናገድ የወሰዱትን ተነሳሽነት በማድነቅ ሁለተኛ ዙር ውይይታቸውን ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በአንካራ ለመቀጠል መስማማታቸውም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም