የግብርና ሥራችንን በማጠናከር በምግብ ራስን ለመቻል እየሰራን ነው - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ሥራችንን በማጠናከር በምግብ ራስን ለመቻል እየሰራን ነው - አርሶ አደሮች
ካራት ፤ ሰኔ 25/2016(ኢዜአ)፡- የግብርና ሥራቸውን በማጠናከር በምግብ ራስን ለመቻል ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋርዱላና ኮንሶ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
አርሶ አደሮቹ በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለማሳካት ጠንክረው እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል በጋርዱላ ዞን ደራሼ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ወንድሙ ወዬሳ በበልግ እርሻ በቆሎ በኩታ ገጠም እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከመኽር እርሻ በተጨማሪ በበልግ እና በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ የማልማት ለምዳቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ሥራቸውን በማጠናከር በምግብ ሰብል ራሳቸውን ለመቻልና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ያነሱት አርሶ አደሩ፣ ለዚህም በአካባቢያቸው በቂ ጸጋዎችና ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል ጠንክረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገልገሎ ከሰሎ፣ በበልግ እርሻ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም ጤፍና ማሽላ ካለሙበት 5 ሄክታር ማሳቸው በሄክታር ከ16 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
"የኩታ ገጠም የግብርና ልማት ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ በጋራ የሚሰራ በመሆኑ በምርታማነት ላይ የተሻለ ተጠቃሚ አድርጎናል" ብለዋል።
በተያዘው የመኸር እርሻ እና በበጋ ወቅት መስኖ ተጠቅመው በኩታ ገጠም በማልማት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር ሳምሶን ማቲዮስ በበኩላቸው "በአካባቢያችን ሰፊ የግብርና አቅም ቢኖርም በአግባቡ ማልማት አለመቻልና በተናጥል መስራታችን ምርቱ ውስን እንዲሆን አድርጓል" ብለዋል።
በምግብ ራሳቸውን ለመቻል ሁሉንም የውሃ አመራጮች በመጠቀም የሰብል እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን በቅንጅት እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ከ111 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በበልግ አዝመራ በበቆሎና ማሽላ መልማቱን ያነሱት ደግሞ የኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ ናቸው።
ከዚህ ውስጥ ከ34 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በኩታ ገጠም መልማቱንና ይህም የአርሶ አደሩን በቅንጅት የመስራት ባህል ማደጉን ከማሳየት ባለፈ ምርታማ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
በመኸርና በበጋ መስኖም ይህንን ጥረት በማጠናከር ከተረጂነት በዘላቂነት ለመውጣት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ይሰራል ብለዋል።
የጋርዱላ ዞን ግብርና መምሪያ የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሽፈራው ግዛቸው በበኩላቸው የግብርና አቅሞችን አማጦ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በዞኑ በበልግ እርሻ ከ45 ሺህ 500 ሄክታር በላይ በሰብል ከተሸፈነ መሬት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።
በተለይ 22 ሺህ 961 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በማሽላና በቦቆሎ ሰብል መሸፈን መቻሉ የዞኑን የግብርና ልማት በጥራትና በምርታማነት ያሳደገ መሆኑን ለዓብነት አንስተዋል።