ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ። 

በግሎባል ኢንቫይሮመንት ፋሲሊቲና በግሪን ክላይሜት ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ዘርፍ እየተተገበሩ የሚገኙ 12 ፕሮጀክቶች ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በዛሬው እለት በቢሾፍቱ ከተማ  መካሔድ ጀምሯል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስዩም መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የአየር ንብረት መዛባት፣ የመሬት መራቆትና የአካባቢ ብክለት የዘመኑ የሰው ልጆች የሥጋት ምንጭ እየሆኑ መጥተዋል። 

ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ በካይ ጋዞችና ሰዎች የተፈጥሮ ኃብትን ለዕለት ተዕለት ፍላጎት ማሟያ በግዴለሽነት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚከሰት የዝናብ እጥረትና ድርቅ በርካታ ዜጎች ለዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች እየተጋለጡና ችግሩም መቀጠሉን ነው ያስረዱት። 

ኢትዮጵያ ከዚህ ችግር በዘላቂነት ለመውጣት የራሷን እቅድ ቀርጻ ተግባራዊ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በቀጣይም ይህንን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። 


 

በግብርና ሚኒስቴር የሲ-አር-ጂ ኢ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ሳምሶን እምሩ በበኩላቸው፡ በፕሮጀክቶቹ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ውኃ አጠር በሆኑ ሥፍራዎች ውኃ የማውጣት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ከአምስት አመት በላይ እንደሆነ የተናገሩት አስተባባሪው፡ አፈጻጸሙም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 


 

ከመንግሥትና ከለጋሽ ተቋማት በሚደረጉ የፋይናንስ ድጋፎች አየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የደን መሬቶች መልሶ ማገገም  ፕሮጀክት አስተባባሪ ሙሉጌታ ወርቁ ናቸው።

የግምገማ መድረኩ በነገም ዕለት ቀጥሎ ይውላል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም