ኢትዮጵያና አዘርባጃን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ያሏቸውን ትብብር ለማጠናከር ይሰራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና አዘርባጃን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ያሏቸውን ትብብር ለማጠናከር ይሰራሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና አዘርባጃን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ያሏቸውን የሁለትዮሽና የባለብዙወገን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋገጡ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ከአዘርባጃን ልዑካን ቡድን አባላት ጋር በአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ መከላከል ዙሪያ ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያና አዘርባጃን በኮንስትራክሽን፣ በቴክኖሎጂ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው።
አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው።
በአከባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ሥራዎች በኩል ከሌሎች አገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን መንግሥት ጋር በጋራ የመሥራት ፍላጎት እንዳላት ለልኡካን ቡድኑ አባላት አረጋግጠውላቸዋል።
ከአዘርባጃን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የአየርን ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለማግኘት በሚደረገው ጥረትም በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ከመጪው የተ.መ.ድ ኮፕ 29 የአየር ንብረት ጉባኤ በፊት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተላለፉት ውሳኔዎች ገቢራዊ እንዲሆኑ በጋራ እንስራለንም ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቋቋም የቅድመ ማስጠንቀቂያ የመረጃ ሥርዓቶችን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የአዘርባጃን ሥነ-ምህዳርና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስትር ሙክታር ባባየቭ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።