የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶው በረራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶው በረራ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፖላንድ ርዕሰ መዲና ወደ ሆነችው ዋርሶው ዛሬ ማምሻውን አዲስ በረራ ጀመረ።
በረራው በሣምንት አራት ቀን ይደረጋል ተብሏል።
በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ አመራሮች፣ በኢትዮጵያ የፖላንድ አምባሳደር ፕርዝማይዝለው ቦባክና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚሁ ጊዜ የበረራው መጀመር የሁለቱን አገራት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱ አገራት በቴክኖሎጂ በግብርና በመሰረተ ልማትና ሌሎችም የትብብር መስኮች በጋራ ለመሥራት የሚያችሉ እድሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ የዚህ በረራ መጀመር ሁለቱ አገራት ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በፍጥነት እያሰፋ ባለበት ወቅት በፖላንድ አዲስ መዳረሻ መጀመር ተጨማሪ ስኬት ነው ብለዋል።
ይህም አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ውስጥ በተለይም በአውሮፖ ገበያ ያለውን ድርሻ ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።
የበረራው መጀመር የሁለቱን አገራት የንግድ ትስስር ለማሳደግና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የፖላንድ አምባሳደር ፕርዝማይዝላው ቦባክ በበኩላቸው፣ የበረራው መጀመር የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ግንኙነት ይበልጥ ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው።