ከተረጂነት አስተሳሰብ የተላቀቀ ማኅበረሰብ በመገንባት የዘመናችንን አድዋ መድገም ይገባል - ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ከተረጂነት አስተሳሰብ የተላቀቀ ማኅበረሰብ በመገንባት የዘመናችንን አድዋ መድገም ይገባል - ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ከተረጂነት አስተሳሰብ የተላቀቀ ማኅበረሰብ በመገንባት የዘመናችንን አድዋ መድገም ይገባል ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት "ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ አገራዊ ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ኃሳብ ውይይት አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ገቢራዊ መደረጉ ይታወሳል።
ፖሊሲው ሥር የሰደደውን የተረጂነት አስተሳሰብ አስወግዶ ወደ ምርታማነት በማሸጋገር እስከ 2030 ለአደጋ ሥጋት የማይበገር ዜጋ መገንባትን ያለመ ነው።
ለዚህ ደግሞ በልመናና ጎዳና ተዳዳሪነት የሚኖሩ ዜጎችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት፣ እርስ በርስ በመረዳዳት መርህ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት የሚያስችል አገር በቀል ተቋምና ሥርዓት መገንባት ላይ ያተኩራልም ተብሏል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ዘርፍ አስተባባሪ ስንታየሁ ወልደሚካኤል (ዶ/ር) ባቀረቡት መነሻ ጽሁፍ፤ ተረጂነት ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ የሚያወርድ ክብረ ነክ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ከተረጅነት አስተሳሰብ በመላቀቅ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ልማት ማረጋገጥና ማኅበራዊ ገፅታ መገንባት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ የያዘችውን በ2030 ለአደጋ ሥጋት የማይበገር ዜጋ የመገንባት ራዕይ እውን ለማድረግ ሁሉም አካላት የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።
በተለይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቃቸው ሕጎች፣ የወጡ ፖሊሲዎች ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ከተረጂነት እንውጣ ሲባል ምንም አይነት ድጋፍ አያስፈልገንም ወደሚል ጽንፍ መሄድ የለብንም ብለዋል።
ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ ችግሮችን በአገራዊ አቅም መመከት አለመቻልና ሥርዓት አለመገንባት ተረጂነትን የሚያባብሱ ሁነቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ከተረጅነት አውጥቶ ረጂ ማድረግ የሚያስችል የልማት ጸጋ ቢኖርም፤ ተረጂነት የጠባቂነት አስተሳሰብ በማንበር እንቅፋት መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የተረጂነት አስተሳሰብ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከምትታወቅበት አድዋ በተቃራኒው እንድትታይ አድርጓታልም ነው ያሉት።
በመሆኑም አገሪቱ ያላትን የሚታረስ ሰፊ የመሬት ኃብት፣ የማዕድን ኃብት፣ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስ ውኃ በመጠቀም ከተረጅነት መውጣት ይገባናል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻል፣ በአረንጓዴ አሻራ 32 ቢሊዬን ችግኝ መትከል መቻል፣ በሌማት ትሩፋትና በኮሪደር ልማት የተሰሩ ሥራዎች በራሳችን አቅም መለወጥ እንደምንችል ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጥንት አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ቅኝ ገዥዎችን በማንበርከክ የተጎናጸፉትን ነፃነት የዘመኑ ትውልድ ከተረጅነት በመውጣት ታሪክ መሥራት አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያን ወደሚመጥናት ክብሯና የተሟላ ነፃነቷ ለመመለስ የተረጂነት አስተሳሰብን አስወግዶ የኢኮኖሚ ነፃነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ የተረጂነት አስተሳሰብ በራስ መተማመንን በመሸርሸር ደካማ የሥራ ባህል ፈጥሯል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ዝቅ አድርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያ መልማት የሚያስችል ጸጋ እያላት በተረጅነት አስተሳሰብ መኖር ሊቆጨንና በቃ ሊባል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ገቢራዊ እንዲሆኑ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በቅንነት መተባበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።