በርካቶችን ለጤና እና ማህበራዊ ችግር እየዳረገ ያለውን ደባል ሱስ የመከላከል ስራ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በርካቶችን ለጤና እና ማህበራዊ ችግር እየዳረገ ያለውን ደባል ሱስ የመከላከል ስራ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016 (ኢዜአ)፦ በርካቶችን ለጤና እና ማህበራዊ ችግር እየዳረገ ያለውን አደገኛ እፅና ደባል ሱስ የመከላከል ስራ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የዓለም ጸረ አደገኛ መድሃኒቶችና እጾች ቀንን በሚመለከት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በባለስልጣኑ የመድኃኒት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስዩም ወልዴ፤ በተለይም በከተሞች በርካታ ወጣቶች ለደባል ሱሶች እየተጋለጡ መሆኑን አንስተዋል።
የልማትና የምርታማነት ጥሩ አቅም የሚባለው በተለይም ወጣቱ ሃይል ለደባል ሱሶችና አደንዛዥ እፅ ተጋላጭ መሆናቸው ለተለያዩ ውስብስብ ችገሮች እየደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሀገርንና ትውልድን እየጎዳ ያለውን የጤና እና ማህበራዊ ችግር የመከላከል ስራ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በባለስልጣኑ በኩልም ለተለያዩ ያልተገቡ ሱሶች የተዳረጉ ወገኖችም ከዚሁ አስከፊ ችግር እንዲወጡ የማገዝና ቀድሞ የመከላከል ስራዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በትምህርት ተቋማት አቅራቢያዎች የሚስተዋሉትን ሱሶችና አዋኪ ተግባራትን የመከላከል ስራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ለዚህም አጠቃላይ በመከላከሉ ሂደት የትምህርት ማህበረሰቡ፣ ወላጆችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የድርሻቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የአደንዛዥ እፅ እና ህገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውርን መግታትና የመከላከል ስራ የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ በተቀናጀ መልኩ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።