ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል አባልነቷ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና ተጫውታለች-ብርጋዴር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል አባልነቷ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና መጫወቷን የምሥራቅ አፍሪካ  የተጠንቀቅ ኃይል ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ ገለጹ።

በኬንያ ናይሮቢ ከሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ቢሮ የተውጣጣ ልዑክ ኢትዮጵያን ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የምታዋጣውን ሞተራይዝድ ሻለቃ የግዳጅ ዝግጁነት የሚያረጋግጥ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። 

ቡድኑ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የቅድመ ዝግጁነት ማረጋገጥና ግምገማ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ እና የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌን ጨምሮ የተጠንቀቅ ኃይሉ አመራሮችና ወታደራዊ መኮንኖች፣ የሲቪል ሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ተወካዮች ተገኝተዋል።



 

ብርጋዴር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ሙያዊነትን የተላበሰና ብቁ ሠራዊት በማዋጣት አይተኬ ሚና አበርክታለች።

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ አስተዋጽዖ በመወጣት የምትታወቅ ሀገር ስለመሆኗም ጠቅሰዋል።

ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ ልምድና ተሞክሮ ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸው፣ እስካሁንም ኢትዮጵያ በተሰማራችበት ተልዕኮ ሁሉ ለነበራት ወሳኝ አበርክቶ ምስጋና ችረዋል። 

በቀጣይም በቀጣናው አገራት ትብብርን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። 

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል  ዓለምእሸት ደግፌ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ለአፍሪካና ለቀጣናው ሰላምና ፀጥታ በትብብር በመሥራት ቁልፍ ሚና የምትጫወት አገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

 

ኢትዮጵያ ለተጠንቀቅ ኃይሉ እንደ መሥራች አገር በእስካሁን ታሪኳ በኃሳብ አመንጪነት ብቻ ሳይሆን በተግባር ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆና መቀጠሏን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ በፋይናንስ ረገድም ትልቅ በጀት መድባ ለቀጣናው ሰላም መስፈን እንደሰራችም ጠቅሰዋል።

የተጠንቀቅ ኃይሉ አቅም እንዲጠናከር ሁሉን አቀፍ ዝግጁነት እንዲኖረውና ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት አንስተዋል።

የቀጣናው አገራት በሁሉም መስክ ዘርፎች ትብብር እንዲጠናከር ተጠንቀቅ ኃይሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ በዚህም የኢትዮጵያ ሞተራይዝድ ሻለቃው ሁልጊዜም ዝግጁ እንደሆነ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው የተሻለ ነገ እንዲመጣና የአካባቢው ህዝብ የሚመኘውን ሰላምና ብልፅግና በዘላቂነት ለማረጋገጥ አይተኬ ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የተጠንቀቅ ኃይሉ ልዑክ በኢትዮጵያ ቆይታው የኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ሞተራይዝድ ሻለቃ ጠቅላይ ጦር ሰፈር ተገኝቶ የሻለቃን ዝግጅትና ቁመና እንደሚመለከትም ይጠበቃል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም