የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የምርምር ውጤቶች ዓለም አቀፍ የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የምርምር ውጤቶች ዓለም አቀፍ የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016 (ኢዜአ)፦ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምርምር ውጤቶች ዓለም አቀፍ የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ገለጹ።
በኢንስቲትዩቱ የበለፀጉ አራት የፈጠራ ውጤቶች ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የባለቤትነት (ፓተንት) መብት ተሰጥቷቸዋል።
የባለቤትነት መብት የተሰጣቸው በሰው ሰራሸ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መሠረት ያደረጉ የስኳር በሽታና፣ የጡት ካንሰር ዓይነቶችን የሚለይ፣ የህፃናት የቆዳ በሽታ ልየታ እና የቡና ቅጠል በሽታ የሚለይባቸው ናቸው።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና፤ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የምርምር እና የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት የባለቤትነት (ፓተንት) መብት የተሰጣቸው የምርምር ሥራዎችም የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ የምርምር ሥራዎቹን ወደ ተግባር ማስገባቱ እንዳለ ሆኖ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የምርምር ሥራዎች ከሀገር ውስጥ ባለፈ ዓለም አቀፍ የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል፤ በበኩላቸው የአዕምሮ ንብረት ጉዳይ የቀጣይ ዘመን የውድድር ዘርፍ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የቀጣይ ትውልድ የውድድር ብቃት ለማሳደግ ጠቃሚ በመሆኑ የላቀ የእውቀት ጥበቃ እንደሚደረግለት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በሰው ሰራሽ አስተውሎት በምርምር እውቀትን አዳብሮ ባለቤትነት (ፓተንት) መብት ማስመዝገቡ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር)፤ የባለቤትነት (ፓተንት) መብት የእውቅና ሰርቲፊኬት የተሰጣቸው የምርምር ውጤቶች በሰው ሰራሸ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
እነዚህም የስኳር በሽታና፣ የጡት ካንሰር ዓይነቶችን የሚለይ፣ የሕፃናት የቆዳ በሽታ እና የቡና ቅጠል በሽታ ልየታ የሚያደርጉ የምርምር ግኝቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።