የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በድሬዳዋ የጎርፍ ስጋት በመቀነስና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ አበርክቷል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በድሬዳዋ የጎርፍ ስጋት በመቀነስና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ አበርክቷል
ድሬዳዋ ፤ሰኔ 24/2016 (ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የድሬዳዋን የጎርፍ ስጋት በመቀነስና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የአስተዳደሩ የግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።
በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደሩ የሥራ ሃላፊዎች ዘንድሮ በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዝግጅት እና ከተረጂነትና ከተመፅዋችነት ለመላቀቅ በተጀመሩ ተግባራት ላይ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በዚሁ ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የድሬዳዋ የጎርፍ ስጋት በመቀነስና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎችን ውጤታማ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ዘንድሮም የሚተከሉት የፍራፍሬ እና ሌሎች ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚያበረክቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ በተለይም ከተረጂነት ለመውጣት የተጀመሩትን ተግባራት የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአስተዳደሩ የአካባቢ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው ዘንድሮ በገጠርና በከተማ የተዘጋጁት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
አስተዳደሩ ለተከላ ካዘጋጃቸው ችግኞች የተወሰኑትን የጎርፍ ተጋላጭ ለሆኑ የምስራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች እና ለሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን በመስጠት ጎርፍን በጋራ የመመከት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ እንደተናገሩት፤ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ እና የአረንጓዴ ልማት ጉዳዮችን በተቀናጀ መንገድ ማሳካት ለድሬዳዋ የህልውና ጉዳይ ነው።
ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት ዘመቻዎች በአካባቢው የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ከማስቻል ባሻገር ፅዱና አረንጓዴ ከተማ ለመፍጠር እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማሳካት አመራሩ በግንባር ቀደምትነት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
የአረንጓዴ አሻራ እና የአረንጓዴ ልማት ተግባራት በተቀናጀ መንገድ ዳር ማድረስ በራስ አቅም ከተረጂነትና ከተመፅዋችነት ለመላቀቅ አይነተኛ ሚና እንደሚያበረክትም አክለዋል ።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአስተዳደሩ የአመራር አባላት በበኩላቸው ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማሳካት በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።