ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በኢንቨስትመንትና በበጎ ፈቃድ ስራዎች አሻራቸውን እንዲያኖሩ ዝግጅት ተደርጓል-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በኢንቨስትመንትና በበጎ ፈቃድ ስራዎች አሻራቸውን እንዲያኖሩ ዝግጅት ተደርጓል-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016(ኢዜአ)፦ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በኢንቨስትመንት፣ በተለያዩ የልማት ስራዎችና የበጎ ፈቃድ ተግባራት አሻራቸውን እንዲያኖሩ ዝግጅት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተለያዩ ዓለም ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትወልድ ኢትዮጵያውያን ክረምቱን ወደ ሀገራቸው በመግባት አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ ዛሬ ከአውስትራሊያና አሜሪካ በ26ኛው የሐረር ቀን በዓል ላይ ለመሳተፍ ለመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአቀባበል ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከሐረሪ ክልል አመራሮች ጋር በመሆን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች አሻራቸውን እንዲያኖሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሶስተኛ ዙር ጥሪ መቅረቡን አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አስታውሰዋል።
ወቅቱ ትምህርት የሚዘጋበት በመሆኑ በርካታ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲያውቁ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሰረት በሐረር ቀን በዓል ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዜጎችን ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ተሳትፏቸው እንዲጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም የልማት ሥራዎችን የሚጎበኙ ሲሆን አሻራቸውን እንዲያኖሩ ምቹ ሁኔታዎች የመፍጠሩ ሥራ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑንም አብራርተዋል።
የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሀኪም ዑመር በበኩላቸው የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራ አባላት የሐረር ቀን በዓልን ከማክበር ጎን ለጎን በተለያዩ በጎ አድራጎት መርሃ ግብሮች እንዲሳተፉ በክልሉ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ነጻ የህክምና አገልግሎት፣ የትምህርት ቤት ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውኑም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ለውጥ ማስመዝገቧን ያነሱት አቶ አብዱልሀኪም፥ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የልማት ሥራዎች ላይ መሳተፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ በሁለት ዙር ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን መጥተዋል።
አሻራዎን ያኑሩ በሚል መሪ ሀሳብ ከሰኔ 20/2016 ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን እንዲያውቁ ለሦስተኛ ዙር ጥሪ መቅረቡንም ጠቁመዋል።
አገራዊ ጥሪው ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ በአካል ቀርቦ ለማየት እድል እንደሚሰጥም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት።
ዛሬ አዲስ አበባ ከገቡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን መካከል በአውስትራሊያ ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት ጀማል መሀመድ(ዶ/ር) ፤ በሙያቸው ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
የኩላሊት እጥበት ክሊኒክ ለማቋቋም ፕሮጀክት መቅረጻቸውንም አመልክተዋል።
በተመሳሳይ ከአውስትራሊያ የመጡት ዱሴት አብዶሽ እና ፈቲሃ አብዱላሂ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የረጅም ጊዜ እቅድ እንደነበራቸው አንስተዋል።
ወደ ሀገራቸው መግባታቸውን ተከትሎም በተለያየ የልማትና ኢንቨስትመንት ስራ ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።