በክልሉ ገበያን ለማረጋጋት የተጀመሩ ውጤታማ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - አቶ አብርሃም ማርሻሎ

ሀዋሳ፤ሰኔ 24/2016 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ገበያን ለማረጋጋት እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ አስታወቁ።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ''የንግድ ሥርዓቱን ዘመናዊ፣ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እንተጋለን'' በሚል  ሀሳብ ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ  የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብረሃም ማርሻሎ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ገበያን ለማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ  የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ ናቸው፡፡

ለዚህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሁሉም ዘርፍ የተደረጉ የተቀናጁ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

እንዲሁም የንግድ ሥርዓቱን መቆጣጠር የሚያስችሉ ህግና አሠራሮችን የማስከበር ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ተግባራቱ የሚቀጥሉ መሆናቸውን ጠቅሰው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደምገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት መኩሪያ በበኩላቸው የንግድ ዘርፍ የተቀመጠለትን ህጋዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲካሄድ በተቀናጀ መልኩ መሠራቱን ተናግረዋል።


 

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የምርት አቅርቦትን የማሳለጥና ህገወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩትን ወደ መስመር ማስገባት የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አንስተዋል።

በዚህም ገበያን ከማረጋጋት ረገድ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው በቀጣይም በተቀናጀ መንገድ በትኩረት እንደሚሰራና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማገዝ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

የዛሬው መድረክም ገበያን ከማረጋጋት ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶችና ተግዳሮቶች ላይ በመወያየት የጋራ አቋም የሚያዝበት ነው  ብለዋል።

በመድረኩም የክልል፣የዞንና ወረዳ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻዎች እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም