ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል አባልነቷ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና ተጫውታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል አባልነቷ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና ተጫውታለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል አባልነቷ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና መጫወቷን የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ገለጸ።
በኬንያ ናይሮቢ ከሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ቢሮ የተውጣጣ ልዑክ ኢትዮጵያን ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምታዋጣውን ሞተራይዝድ ሻለቃ የግዳጅ ዝግጁነት የሚያረጋግጥ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል።
ቡድኑ በዛሬው ዕለት የቅድመ ዝግጁነት ማረጋገጥና ግምገማ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ነው።
የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ እና የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌን ጨምሮ የተጠባባቂ ኃይሉ አመራሮችና ወታደራዊ መኮንኖች፣ የሲቪል ሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ተወካዮች ታድመዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ፖል ካሁሪያ ጀማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሙያዊነት የተላበሰና ብቁ ሠራዊት በማዋጣት አይተኬ ሚና እንደነበራት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ አስተዋጽዖ በመወጣት የምትታወቅ ሀገር ስለመሆኗም ጠቅሰዋል።
ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ ልምድና ተሞክሮ ያላት ሀገር መሆኗንም ገልጸው፣ እስካሁንም ኢትዮጵያ በተሰማራችበት ተልዕኮ ሁሉ ለነበራት ወሳኝ አበርክቶ ምስጋና ችረዋል።
በቀጣይም በቀጣናው አገራት ትብብርን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ለአፍሪካና ለቀጣናው ሰላምና ፀጥታ በትብብር በመሥራት ቁልፍ ሚና የምትጫወት አገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለተጠባባቂ ኃይሉ እንደ መሥራች አገር በእስካሁን ታሪኳ ኃሳብ አመንጪነት ብቻ ሳይሆን በተግባር ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በፋይናንስ ረገድም ትልቅ በጀት መድባ ለቀጣናው ሰላም መስፈን እንደሰራችም ጠቅሰዋል።
የተጠባባቂ ኃይሉ አቅም እንዲጠናከር ሁሉን አቀፍ ዝግጁነት እንዲኖረውና ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት አንስተዋል።
የቀጣናው አገራት በሁሉም መስክ ዘርፎች ትብብር እንዲጠናከር ተጠባባቂ ኃይሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ በዚህም የኢትዮጵያ ሞተራይዝድ ሻለቃው ሁልጊዜም ዝግጁ እንደሆነ ገልፀዋል።
በቀጣናው የተሻለ ነገ እንዲመጣና ሰላምና ብልፅግና እንዲረጋገጥ የነበረውን አይተኬ ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የተጠባባቂ ኃይሉ ልዑክ በኢትዮጵያ ቆይታው የኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሞተራይዝድ ሻለቃ ጠቅላይ ጦር ሰፈር ተገኝቶ የሻለቃን ዝግጅትና ቁመና እንደሚመለከትም ይጠበቃል።