የአካል እንቅስቃሴን ባህል በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል- ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
የአካል እንቅስቃሴን ባህል በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል- ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2016(ኢዜአ)፦ የአካል እንቅስቃሴ ተግባራትን ባህል በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
20ኛው አለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በእግር ጉዞ ፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴና ደም ልገሳ መርሐግብር ተከብሯል።
መርሐግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የሚተካውን ደም በልግስና የማይተካውን የሰው ህይወት የምናተርፍበት በመሆኑ ደም ለጋሾች ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ደም መለገስ ባህላችን መሆን አለበት ያሉት ሚኒስትሯ ቀኑን የምናከብረው በደም እጦት ምክንያት ዜጎቻችን ህይወታቸዉን እንዳያጡ ደም መለገስን ባህላችን እንድናደርግ ለማስተማር ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ዛሬ በእርምጃ ቀኑን እያሰብን፣ ደም እየለገስን የሰው ህይወትን እያተረፍን እንቀጥላለን ያሉት ሚኒስትሯ ይህ የእግር ጉዞ በየወሩ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ዶክተር መቅደስ አክለውም በእርምጃ፣ በአካል እንቅስቃሴ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንም እንከላከላለን ማለታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ደም እና ህብረህዋስ ባንክ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እጅግ ወሳኝ የህክምና ግብአት የሆነው ደም ለማሟላት ሰዎች በቋሚነት ደም መለገስ ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ይህ ቋሚ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን የምናመሰግንበት እና አዳዲስ ደም ለጋሾችን ለማፍራት ግንዛቤ የምናሰፋበት እለት ነው ያሉት ዶክተር አሸናፊ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነፍሶችን ለመታደግ ደም የለገሳችሁ ሁሉ እናመስግናለን በማለት ምስጋና አቅርበዋል።
ለ60 ኛ ጊዜ የደም ለጋሽ የሆኑት አቶ ዳዊት ፍቅሩ መርሐግብሩ የህብረተሠቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በእጅጉ እንደሚጠቅም ገልጸው ህብረተሠቡ ደም በመለገስ ክቡር የሆነውን የሠው ህይወት ሊታደግ ይገባል ብለዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች፣ የሆስፒታል ስራ አስኪያጆች፣ የደምና ህብረህዋስ ባንክ ሠራተኞችና ሀላፊዎች፣ ማህበራት እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን ደም ለመለገስ በተዘጋጁ ቦታዎች በመገኘት ከ 350 በላይ ዩኒት ደም ለግሰዋል።