ህብረተሰቡ ደም በመለገስ ህይወት የማዳን በጎ ተግባርን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- ዶክተር መቅደስ ዳባ  

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2016 (ኢዜአ)፡- ህብረተሰቡ ደም በመለገስ ህይወት የማዳን በጎ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ጥሪ አቀረቡ።

የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ለለገሱት ክቡር ደም እና ለታደጉት ህይወት ክብርና ምስጋና ለመስጠት በየዓመቱ ሰኔ 7 የደም ለጋሾች ቀን ሆኖ እንዲከበር  እ.እ.አ በ2004 መወሰኑ ይታወሳል። 

ዕለቱ  ሁለንተናዊ ደህንነቱ የተጠበቀ የደም ተደራሽነትን በማረጋገጥ ህይወትን ለመታደግ ለሚደረግ ጥረት ትኩረት እንዲሰጥ ንቅናቄ የመፍጠር ዓላማን ያነገበ ነው። 

ዘንድሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ  የደም ለጋሾች ቀን ለ20ኛ ጊዜ "ደም እንለግስ፣ ህይወት እናጋራ፣ ዘወትር እናጋራ" በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል። 

የኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ቀኑን ለደም ለጋሾች ማህበራት፣ ክበባት፣ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋናና ዕውቅና በመስጠት በአዲስ አበባ አክብሯል።

በመርሃ ግብሩ  ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፥ ደም ልገሳ ከራስ ህይወት አካፍሎ የሌሎችን ህይወት የማዳን ውድ ስጦታ ነው።


 

ከዚህ አኳያ በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸው አደጋ ላይ ለሚገኙ ህሙማን ደማቸውን የሚለግሱ ወገኖች ሊመሰገኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ ሀገር የደም ባንክ ተቋቁሞ እየሰራ የሚገኘው እናቶች ህጻናትና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸው እንዳያልፍ ለማድረግ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የደም ልገሳ አገልግሎትን ከአጠቃላይ የጤና ስርዓቱ ጋር በማስተሳሰር ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም ሁሉም ህብረተሰብ በየአካባቢው ደም በመለገስ ህይወት የማዳን በጎ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ታዘበው ታየ (ዶ/ር)  በበኩላቸው፥ በደም ለጋሽ በጎ አድራጊዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ህሙማንን ህይወት መታደግ  መቻሉን  ተናግረዋል። 

ይህን እንጂ አሁንም በድንገተኛ አደጋ፣ በወሊድና በተለያዩ ምክንያቶች  ደም የሚያስፈልጋቸው በርካታ ወገኖች መኖራቸዉን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ጤነኛ የሆኑና እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ደም እንዲለግሱ ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም