ለ26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን ለመሳተፍ ወደ ሀገር ቤት የገቡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለ26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን ለመሳተፍ ወደ ሀገር ቤት የገቡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል ተደረገ
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 24/2016 (ኢዜአ)፡- ለ26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን ለመሳተፍ ከተለያዩ አለማት ወደ ሀገር ቤት የገቡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያደረጉትን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል እንዲሁም በ26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን በዓል ላይ ለመሳተፍ ወደ ሀገር ቤት የመጡ ዲያስፖራዎች ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በፌደራልና በክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በርካታ ሀረሪዎችና የሀረር ተወላጆች ሀገራዊውን ጥሪ በመቀበልና በ26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ አለማት ወደ ሀገር ቤት የገቡ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ወደ ሀገር ቤት እየተመሙ ይገኛሉ ሲል ከሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በአቀባበሉ ላይም የሀረሪ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማእከል ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሊድ አልዋን፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው ፣ የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሀኪም ኡመርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።