የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በጅቡቲ ሆራይዘን ነዳጅ ተርሚናል ስራ አስፈፃሚ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በጅቡቲ ሆራይዘን ነዳጅ ተርሚናል ስራ አስፈፃሚ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2016 (ኢዜአ)፦ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከጅቡቲ ኢነርጂ ሚኒስትር ዮኒስ አሊ ጉዴ ጋር በመሆን ከሆራይዘን የነዳጅ ተርሚናል ስራ አስፈፃሚ ኦማር ሀሰን ጋር ተወያዩ።
ውይይቱ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በሚደረገው ዕለታዊ የነዳጅ ዝውውር ላይ ጅቡቲ ያለው የሆራይዘን የነዳጅ ተርሚናል ሳይታደስ በመቆየቱ ምክንያት ተጨማሪ የጥገና አገልግሎት የሚያስፈልገውና እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት ከማሟላት አንጻር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የነዳጅ ፍላጎት ከግምት ያስገባ አቅርቦት ማስፈለጉን የገለጹት አቶ አህመድ፤ በተርሚናሉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚወሰዱ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ሃሳብ ሰጥተዋል።
ሚስተር ኦማር ሀሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ የነዳጅ ተርሚናሉን ለመጠገን እና ለማስፋፋት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ ሁለቱም ሚኒስትሮች በቀጣይ የነዳጅ ተርሚናሉን የአቅርቦት አፈጻጸም የሚከታተል ቴክኒካል ኮሚቴ ለማዋቀር እና በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት መስማማታቸውን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል።