ቀጥታ፡

በክልሉ  የደም ባንክ አገልግሎትን ለማዳረስ በተደረገው ጥረት  ውጤታማ ስራ መከናወኑ ተገለጸ

ባህርዳር ፤ ሰኔ 23/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የደም  ባንክ አገልግሎትን  ለማዳረስ  በበጀት ዓመቱ በተደረገው ጥረት ውጤታማ ስራ መከናወኑን  የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

የደም ለጋሾችን ቀን በባህር ዳር  ከተማ ዛሬ ተክብሯል።

በዚህ ወቅት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ  አበበ ተምትም ፤ በክልሉ 10 የደም ባንኮችን በማቋቋም አንድም ሰው በደም እጥረት እንዳይጎዳ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በየአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን በማፍራትና ነባሮችን በደንበኝነት ይዞ በመዝለቅ እናቶች፣ ህጻናትና ሌሎች ደም የሚያስፈልግቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት መታደግ መቻሉን ገልጸዋል።


 

ይህም በበጀት ዓመቱ በአማካይ 160 ሺህ ለሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት እንደሆነ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታየ በበኩላቸው፤  የባህር ዳር ደምና ህብረ ህዋስ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ በተከታታይ አርአያነት ያለው ተግባር በመፈጸም ተሸላሚ ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የበጎ ፍቃደኛ ደም  ጋሽ የህብረተሰብ ክፍል ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤የህብረተሰቡ የተለመደውን ልገሳውን  አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የባህር ዳር ደምና ህብረ ህዋስ አገልግሎት ሃላፊ አቶ ምክሩ ሽፈራው እንዳሉት፤ደም ከበጎ ፍቃደኞች በመሰብሰብ ለጤና ተቋማት በማስተላለፍ  በደም እጦት ምክንያት የሰው  ህይወት እንዳያልፍ ሲከናወን የቆየው ስራ አበረታች ነው።

የህብረተሰቡ ደም የመለገስ ፍላጎት እያደገ እንደመጣ የገለጹት አቶ  ምክሩ፤  ይህ ደግሞ በዋጋ የማይተመነውን የሰው ህይወት የማትረፍና ከሰብአዊነት  የመነጨ ስጠታ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ  ከደም መሰብሰብ በተጨማሪ የዐይን ባንክ አገልግሎት አቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱንም ጠቅሰዋል።

የደም ለጋሾችን ቀን የክልሉ ጤና ቢሮና የደም ባንክ አመራር አባላትና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ  ተከብሯል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም