ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቆይታችን አስደሳች እና ሀገሪቱም በፈጣን ለውጥ ላይ መሆኗን የተገነዘብንበት ነው - የናይጀሪያ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቆይታችን አስደሳች እና ሀገሪቱም በፈጣን ለውጥ ላይ መሆኗን የተገነዘብንበት ነው ሲሉ የናይጀሪያ የቀድሞ ታላላቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ተናገሩ፡፡

የቀድሞው የናይጀሪያ የእግር ኳስ ኮከብ ንዋንኩ ካኑን ጨምሮ የቀድሞ የአህጉሪቱ ታላላቅ ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል ለመታደም አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

በቆይታቸውም ከፌስቲቫሉ በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ዛሬ ማለዳ ደግሞ በወዳጅነት ፓርክ በመገኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን፤ በስፍራው ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡


 

የቀድሞው የናይጀሪያ እግር ኳስ ኮከብ ንዋንኩ ካኑ በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ እጅግ ውብና የሚያስደንቅ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን ተናግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታችን የተደረገልን አቀባበልና እንክብካቤ ቤታችን ያለን ያህል እንዲሰማን አድርጓል ያለው የናይጀሪያ የቀድሞ እግር ኳስ ኮከብ፤ በቀጣይም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ እንደሚመጣ ያለውን እምነት ገልጿል፡፡

በቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ራዕይ መሰረት አድርገው እያከናወኗቸው ያሉ የልማት ስራዎችን ስለመጎብኘታቸውም ተናግሯል፡፡


 

ሌላኛው የናይጀሪያ የቀድሞ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ታሪቦ ዌስት፤ በቆይታቸው የተለያዩ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገር ባለፈ ለአፍሪካ ያላቸውን ራዕይ እንደሚያሳዩ ተገንዝቤያለሁ ነው ያለው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ዋንጫን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ በማድረግ የሀገሪቱን እግር ኳስ የማነቃቃት እቅድ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ይህ እውን እንደሚሆን ያለውን መልካም ምኞት ገልጿል፡፡

የቀደሞ የአህጉሪቱ ታላላቅ ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውም ከኢትዮጵያውያን ጋር ትስስር በመፍጠር የእግር ኳስ ባህል እንዲሻሻል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግሯል፡፡


 

በቆይታችን ኢትዮጵያውያን በክብርና በፍቅር ተቀብለውናል ያለው ደግሞ ሌላኛው የቀድሞ እግር ኳስ ኮከብ ዳንኤል አሙካቺ ነው፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ካደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ በተጨማሪ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መሳተፋቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረበትም ነው የገለጸው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ዳግም በሚመጣበት ወቅትም የተከላቸውን ችግኞች እንደሚንከባከብ ነው ያረጋገጠው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም