ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል ላይ ለመታደም ከመጡ ዕውቅ እና አንጋፋ የቀድሞ የአፍሪካ እግር ኳስ ተጫዋቾች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ ውስብስብ ሂደቶችን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም ጥያቄዋ ዕውን እንዲሆን ጥረት እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።

ከወቅቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ጋርም በጉዳዩ ላይ ውይይት ስለመደረጉ ጠቁመዋል፡፡


 

የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከማነቃቃት ባሻገር ለገጽታ ግንባታ እና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ አፍሪካ ታላላቅ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውም ይህንን የኢትዮጵያ ውጥን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ታላቁ ሩጫ የኢትዮጵያን ገጽታ በማሳየት የነበረውን ጉልህ ሚና ጠቅሰው፤ በቀጣይም የፈረስ ጉግስን ጨምሮ በተለያዩ ስፖርት ዘርፎች የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

አፍሪካ ታላላቅ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን በወዳጅነት ፓርክ የአረንጓዴ አሻራቸውንም አሳርፈዋል፡፡ 

የቀድሞው የናይጀሪያ ኮከብ ተጫዋች ንዋንኩ ካኑን ጨምሮ የቀደሞ የአህጉሪቱ ታላላቅ ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል ላይ ለመታደም አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

በቆይታቸውም ከፌስቲቫሉ በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም