"መቻል ለኢትዮጵያ" የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝቡ ለክለቡ ያለውን አጋርነት ያሳየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
"መቻል ለኢትዮጵያ" የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝቡ ለክለቡ ያለውን አጋርነት ያሳየበት ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2016(ኢዜአ)፦ "መቻል ለኢትዮጵያ" የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝቡ ለክለቡ ያለውን አጋርነት ያሳየበት እንደሆነ የመቻል ስፖርት ክለብ ገለፀ።
መነሻውን እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው "መቻል ለ ኢትዮጵያ" የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል።
የጎዳና ላይ ሩጫውን በወንዶች አትሌት በላይ ዝቁ አስፋው እና በሴቶች አትሌት መቅደስ ሽመልስ አሸንፈዋል፡፡
በወንዶች ውድድር ጠንካራ ፉክክር ያደረገው የመቻል ስፖርት ክለብ አትሌቱ ጌታነህ ሞላ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን ደሞዝ በቀለ በሶስተኛነት ውድድሩን ጨርሷል፡፡
በሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫን አትሌት መቅደስ ሽመልስ አንደኛ በመውጣት ስታሸንፍ አትሌት መብራት ግደይ ሁለተኛ፤ ወርቅውሀ ጌታቸው (ከመቻል ስፖርት ክለብ) በሶስተኝነት አጠናቀዋል።
በሩጫ መርሐ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ሃላፊ ሌተናል ጀነራል አለምሸት ደግፌ፤ ስፖርት ጤናማና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ መከባበርን እና የሰው ልጆች ሁሉ እኩልነትን በመስበክ ጥላቻንና መቃቃርን የሚያስወግድ ማህበራዊ ሁነት እንደሆነም ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ ሀገርን አስከብሮ ማስቀጠሉን ገልጸው፥ ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ የስፖርት ዕድገት ውስጥም መቻል ስፖርት ክለብን በማቋቋም ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።
በኦሎምፒክ የመጀመሪያ ወርቅ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ያስገኘው ሻምበል አበበ ቢቂላ የመቻል ስፖርት ክለብ ትሩፋት እንደሆነ ጠቀሰዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት ውድድር መድረኮች ለተቀዳጀቻቸው ድሎች መቻል ስፖርት ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከተም አስታውሰዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ባሻገር የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ ብርቅዬ አትሌቶችንና እግር ኳስ ተጫዋቾችን ያፈራ ተቋም መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህ ስፖርት ክለብ ወደ ቀድሞ የመወዳደር አቅሙ ተመልሶ በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስና ሌሎችም ውድድሮች የኢትዮጵያ ስም ከፍ አድርጎ ለማስጠበቅ የስፖርቱ ቤተሰብ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የመቻል ስፖርት ክልብ ለሀገራችን ስፖርት ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ የመጣ ነው ብለዋል።
መቻል በአትሌቲክስ ስፖርት ዘመን የማይሽራቸው ብርቅዬ እና ድንቅ አትሌቶች ካፈሩ ክለቦች ግንባር ቀደም እንደሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑንም የስፖርት ማህበረሰቡ ክለቡን በመደገፍ ወደ ቀድሞ የአሸናፊነት ታሪኩ ለመመለስ ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ ቦርድ ሰብሳቢ ሰይፉ ጌታሁን (ዶ/ር) የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው ብለዋል።
በዛሬ ዕለት በተካሄደው "መቻል ለ ኢትዮጵያ" የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሳተፋቸውን ገልፀዋል።
በዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ የስፖርቱን ማህበረሰብ ጨምሮ መላው ህዝብ ከመቻል ስፖርት ክለብ ጎን መሆኑን አሳይቷል ነው ያሉት።