ቀጥታ፡

ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 250 ተማሪዎችን አስመረቀ

ቦንጋ፤ ሰኔ 23/2016(ኢዜአ)፦ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 250 ተማሪዎች አስመረቀ።

ከተመራቂዎቹ መካከል 34 ምሩቃን ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ሳይንስ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸው መሆኑም ተገልጿል።

ከአጠቃላይ ምሩቃን መካከልም 142 በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው። 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም የአካባቢውንና የሀገሪቱን የልማት ፍላጎት የሚመልስ የሰው ሀይል የማቅረብ ሀላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አካባቢው የሚታወቅበትን የቡና ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ጴጥሮስ፣ ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የቡና ሳይንስ ተማሪዎች ዛሬ ማስመረቁን ገልጸዋል።

ይህም ሀገሪቱ በቡና ልማት ባላት እምቅ ሀብት ላይ የተሻለ ስራን በመስራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቡና ሳይንስ ዘርፍ ከመጀመሪያ ዲግሪ በተጨማሪ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር 11 ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ በዘርፉ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ለማሰልጠን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርቃው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ሀይሌ፣ በበኩላቸው ተመራቂዎች በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው ለዛሬ ቀን በመድረሳቸሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን በማህበረሰብ አገልግሎት አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ ያከናወናቸው ተጨባጭ ሥራዎች በሀገር ደረጃም እውቅና ያገኙ በመሆናቸው ክልሉና ዩኒቨርሲቲው ተቀራርበው በመስራት ሊያጠናክሩት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ምሩቃኑ በሰለጠኑበት ሙያ ህዝብና ሀገርን በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉም ዶክተር መኩሪያ አሳስበዋል።

ከተመሰረተ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም