በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ የሚያነሳውንና ከሊጉ የሚወርደውን ክለብ ሊጠቁሙ የሚችሉ ወሳኝ ጨዋታዎች ያደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ዋንጫውን ለማንሳትና ከሊጉ ላለመውረድ በሚደረገው ፋክክር ላይ ጉልህ ተጽእኖ ያላቸው ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሻሸመኔ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ነጥብ  ተጋርቷል፤ በጨዋታዎቹ 11 ጎሎችን ሲያስቆጥር 4 ግቦችን አስተናግዷል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ58 ነጥብና በ26 የግብ ክፍያ ሊጉን በአንደኝነት እየመራ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሻሸመኔ ከተማ በበኩሉ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል፤ በእነዚህ ጨዋታዎች 5 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 11 ግቦችን አስተናግዷል።

በዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ የሚሰለጥነው ሻሸመኔ ከተማ በ14 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በ29ኛው ሳምንት ሌላኛው መርሐ ግብር አዳማ ከተማ ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ  በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል፤ 1 ጊዜ ደግሞ  አቻ ወጥቷል።

በ5ቱ ጨዋታዎች 11 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ግቦችን ያስተናገደው አዳማ ከተማ፤ በሊጉ በ44 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የዋንጫ ተፎካካሪው መቻል ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች 12 ጎሎችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 5 ጎሎችን አስተናግዷል።

በገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በ57 ነጥብና በ16 የግብ ክፍያ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ መቻል 2 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም።

የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መቻል በዛሬ ጨዋታዎች ላይ የሚያስመዘግቡት ውጤት የፕሪሚየር ሊጉን አሸናፊነት ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።

በሌላ በኩል ሀምበሪቾ ከወልቂጤ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ የሚመራው ሀምበሪቾ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 4 ጊዜ  ተሸንፎ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በነዚህ 5 ጨዋታዎች ቡድኑ 1 ግብ ብቻ ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል።

በ28ኛ ሳምንት ከፕሪሚየር ሊጉ የወረደው ሀምበሪቾ በ9 ነጥብ በ16ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች 3 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ግቦች ተቆጥረውበታል።

በሙሉጌታ ምህረት የሚሰለጥነው ወልቂጤ ከተማ በ17 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሻሸመኔ ከተማ እንዲሁም ሀምበሪቾ ከወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ ሰዓት የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ሀምበሪቾን ተከትሎ ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚወርደውን ክለብ ሊለይ ይችላል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች  ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና አንድ አቻ ሲለያዩ የወላይታ ድቻና ፋሲል ከነማ ግጥሚያ ምንም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም