የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን በማሳደግ ለስርዓተ ምህዳር ደህንነት መጠበቅና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ሚና አለው - አቶ ከበደ ይማም - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን በማሳደግ ለስርዓተ ምህዳር ደህንነት መጠበቅና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ሚና አለው - አቶ ከበደ ይማም
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን በማሳደግ ለስርዓተ ምህዳር ደህንነት መጠበቅና ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ በይፋ አስጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ለኢዜአ እንዳሉት፥ ድህነትን በመቀነስ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የተፈጥሮ ሀብትን በተገቢው መንገድ መጠበቅና መጠቀም ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል የደን ሀብት በአግባቡ ባለመጠበቁ እንዲሁም ለመጠለያ ግንባታና ለማገዶ እንጨት በመጨፍጨፉ ለረጅም ዓመታት ተመናምኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በፈረንጆቹ ከ2000-2013 በተደረገ ጥናት በዓመት በአማካይ 92 ሺህ ሄክታር ደን ይጨፈጨፍ እንደነበር ገልጸው፥ ከ2014-2019 በተደረገ ጥናት ደግሞ የደን ጭፍጨፋ ወደ 38 ሺህ ሔክታር ዝቅ ማለቱን አንስተዋል።
አሁን ላይ በዓመት የደን ጭፍጨፋ የሚፈጸምበት ከባቢ ወደ 27 ሺህ 703 ሄክታር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በተገቢው መንገድ ያልያዙ እና ጥቅም ላይ ያላዋሉ ሀገራት ላልታሰበ ሥርዐተ-ምዳራዊ አደጋ መጋለጣቸውንም ጠቅሰዋል።
የደን ለበስ መሬቶች መራቆት፣ ሚዛን ያልጠበቀ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለተጠቀሰው አደጋ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከ40 በመቶ ወደ 3 በመቶ አሽቆልቆሎ እንደነበር የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ሽፋኑ 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ለደን ሽፋኑ ከፍ ማለት ወሳኝ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ ልማት የደን ሽፋንን በማሳደግ ለስርዓተ ምህዳር ደህንነት መጠበቅና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የደን ልማት ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን እየጨመረ መጥቷል።
ይህም የሆነው ህብረተሰቡ ስለ ደን አስፈላጊነት ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱና ችግኞችን በአግባቡ የመንከባከብ ባህል በማደጉ ነው ብለዋል።
የማገዶ እንጨትን የሚተኩ የሀይል አማራጮች እያደጉ መምጣትና ለግንባታ የብሎኬትና ጡብ ምርት እየተስፋፋ መሆኑ የደን ጭፍጨፋን በመቀነስ የአረንጓዴ ልማቱን ይበልጥ እያጠናከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን በዚህም አጠቃላይ የተተከሉ ችግኞችን ብዛት 40 ቢሊዮን ለማድረስ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ ቀርቧል።