የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በ2016 በጀት ዓመት በሠራው የወንጀል ምርመራ መዝገብ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በ2016 በጀት ዓመት በሠራው የወንጀል ምርመራ መዝገብ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለፀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በ2016 በጀት ዓመት በሠራው የወንጀል ምርመራ መዝገብ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ተገለፀ።
ይህ የተገለጸው ጠቅላይ መምሪያው በ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ በተከናወነበት ወቅት ነው።
የበጀት አመቱን የማጠቃለያ የስራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የመሩት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ናቸው።
በዚህም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና ዜጎች ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን እንዲመሩ ለማስቻል በህግ የተሰጠውን ወንጀልን በመከላከል የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ እና ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝም ሰብአዊ መብትን ባከበረ መልኩ መርምሮ ለህግ የማቅረብ ተልዕኮውን በሚገባ እየተወጣ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተጀመረው እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ የፀጥታው ዘርፍ አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ በወንጀል መከላከልም ሆነ በወንጀል ምርመራ ስራ ብቁ ሆኖ ለመገኘት እንደተቋም ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ተግባራትን በማከናወን ሀገራዊ ተልዕኮውን በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ከነበሩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በመነሳት በ2016 በጀት ዓመት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት የበጀት አመቱን ዕቅድ አዘጋጅቶ ሲሰራ እንደቆየም ገልፀዋል።
በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በበጀት አመቱ 7 ሺህ መዝገቦች ማደራጀት መቻሉን አስታውቀዋል።
በዚህም 5 ሺህ 822 የምርመራ መዝገቦችን በማጠናቀቅ ለሚመለከተው የፍትህ አካል የተላኩ ሲሆን 1 ሺህ 204 መዝገቦች ደግሞ በምርመራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች እየተንከባለሉ ወደ 2016 በጀት ዓመት የዞሩ የምርመራ መዝገቦች ላይ በተሠራው የማጥራት ሥራ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም ጠቁመዋል።
በዚህም ከ7 ሺህ 26 ወደ 1 ሺህ 200 የምርመራ መዝገቦች ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረው በሪፎርሙ በተፈጠረው የቴክኖሎጂ አቅምና በጠንከራ የመፈፀም ብቃት የተገኘ ውጤት መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
በበጀት ዓመቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ 623 የምርመራ መዝገቦች ላይ በ1ሺህ 155 ተከሳሾች ላይ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎች እንዲተላለፉ መደረጉን አስታውቀዋል።
በዚህም ከሁለት ወር እስከ ዕድሜ ልክ ማስፈረድ የተቻለ ሲሆን ከ500 ብር እስከ 11 ሚሊየን ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔም የተላለፈባቸው መሆኑን አንስተዋል።
በርካታ የተለያዩ የኮንትሮባንድ መኪናዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን በታክስና ጉምሩክ የማጭበርበር ወንጀል ከ58 ቢሊዮን ብር በላይ በመንግስት ላይ የደረሰ ጉዳት ላይ ምርመራ ሲደረግ ቆይቷል ተብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በተለይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ በወንጀል ድርጊት በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ውጤታማ ሕግ የማስከበር ተግባር መከናወኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በአደገኛ ዕፅ ዝውውር ወንጀል120 የሚደርሱ የተለያየ የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነም በግምገማው መነሳቱን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የፎረንሲክ ወንጀል ምርመራም ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና በሰለጠነ የሰው ኃይል በመታገዝ በተሠራው ውጤታማ ሥራ በበጀት ዓመቱ ከ281 ሺህ 151 በላይ የፎረንሲክ ምርመራ አገልግሎት በመስጠት ከ20 ሚሊየን ብር በለይ ገቢ ማሰባሰብ መቻሉም ተገልጿል።