ቀጥታ፡

መጠላለፍና መገዳደል ችግርን ለቀጣይ ትውልድ ከማስተላለፍ ውጪ ጥቅም የለውም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦መጠላለፍና መገዳደል ችግርን ለቀጣይ ትውልድ ከማስተላለፍ ውጪ ጥቅም የሌለው በመሆኑ ትውልዱ ተቀራርቦ በመስራት ድህነትን ለማሸነፍ መትጋት እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በደሴ ከተማና አካባቢው እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት "የምትተክል ሀገር፤ የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ አብረን በመትከል ለልጆቻን የሚበጅ ነገር ለመተው ዕድል ስላገኘን ከፍተኛ ክብርና ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

ወሎ በገራገርነቱ ይታወቃል፤ የደጋግ ህዝብ መኖሪያ መሆኑም ታሪኩ ይናገራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የወሎ ህዝብ ሰላም ወዳድ እና በአብሮነት የሚታወቅ አቃፊ መሆኑን ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ ከንቲባ ህዝቡን በማስተባበር የጀመሩት አበረታች ውጤት ምክንያት ደሴ በዳቦ ፋብሪካ ሀይቅ ደግሞ በገበታ ለሀገር ተመርጠው በተሻለ የልማት ግንባታ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ልማት ለኢትዮጵያ በእጅጉ የሚያስፈልግ በመሆኑ ሁሉም ለልማት መተባበርና መረባረብ እንዳለበት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ምንም ደሃ ብንሆን አፍሪካ በቅኝ ስትገዛ ሉዓላዊነታችንን ያስከበርን ህዝቦች ነን ብለዋል።

ቀደምት አባቶች የሀገርን ሉዓላዊ አንድነት ለማስከበር ያስመዘገቡት አኩሪ ገድልም በዚህ ትውልድ ድህነትን በማሸነፍ የሚደገም መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ለዚህም ስላም፣ አብሮ መስራትና ትብብር አስፈላጊ በመሆኑ በግራም ሆነ ቀኝ የወጡ ወንድሞቻችንን መክራቹህ መልሱ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ባልተገባ መንገድ የሚደረግ ጉዞ ምንም አይነት ውጤትና ድል የማያስገኝ በመሆኑ በትብብር መልካም ሀገርን በመገንባት የጸናች ኢትዮጵን ለልጆቻችን እናስረክባለን ብለዋል።

መጠላለፍ፣ መባላትና መገዳደል ችግርን ለቀጣይ ትውልድ ከማስተላለፍ ውጪ ጥቅም እንደሌለው አስገንዝበዋል።

ማንኛውም አካል በይቅርታ፣ በመተውና በጋራ ሀገር በመገንባት መንፈስ ለመስራት ዝግጁ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

ከጥፋት ይልቅ ሰላምና አንድነትን በማስፈን ሂደት የወሎ ሽማግሌዎችና እናቶች ልጆችን በመምከርና በማስታረቅ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና ሀገር እንድትሆን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያን ለማስተዳደርና ለማገልገል የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠንን አደራ በከፍተኛ ትጋት፣ ታማኝነትና ቅንነት በመስራታችን ሀገራዊ ስኬት እየተመዘገበ መጥቷል ብለዋል።

በዚህም ሰላም እና ልማትን ጨምሮ በሁሉም መስክ ዝግጁዎች መሆናችን መታወቅ አለበት ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ ክልሉ ከነበረበት የጸጥታ ችግር ወጥቶ የተሻለ የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የደሴ እና የአካባቢው ማህበረሰብም የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲያደርጉት የቆዩትን ስኬታማ ስራ አድንቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሃብት ፈጠራ ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው የክልሉን የልማት ስኬት ለማደናቀፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማና አካባቢው በነበራቸው ቆይታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም