ችግኝ መትከል ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ኢንቨስትመንት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ችግኝ መትከል ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ኢንቨስትመንት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ ችግኝ መትከል ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ኢንቨስትመንት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ሀይቅ ከተማ ተገኝተው የዘንድሮን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ዘንድሮ "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ ከ7 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ይገኛል።
ይህም ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን ቁጥር ከ40 ቢሊየን በላይ እንደሚያደርሰው ገልጸዋል።
መንግስትና ህዝብ ልመና ይብቃን በማለት ባለፉት ዓመታት በርካታ ስራዎችን ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በምግብ እራሳችንን ለመቻል በሰራነው ስራ በግብርናው ዘርፍ አመርቂና ዓለም የተደነቀበትን ተግባር መፈጸም ጀምረናል ብለዋል።
ይህ የግብርና ስራ ጸንቶ ውጤታማነቱ መቀጠል የሚችለው ግን በተከታታይ ችግኝ መትከል ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ችግኝ መትከል ሀገርን አረንጓዴ ከማልበስ ባለፈ በሁሉም ዘርፎች ለሚሰሩ ስራዎች ጉልበት የሚጨምር መሆኑን ተናግረዋል።
በየጊዜው ችግኝ የምንተክለው በግብርና የጀመርነውን ስራ በውጤታማነቱ ለማጽናትና ለማስቀጠል ካለን ጽኑ መሻት ነው ብለዋል።
ችግኝ መትከል ኢትዮጵያ ቢኢነርጂ ልማት የምታከናውነውን ስራም በእጅጉ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ በተለይ በታዳሽ ኃይል ብዙ ሀብት እያፈሰሰች መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሚገነቡ ግድቦች በኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሀብትና ላብ የሚሰሩ በመሆኑ ከሌለን ሀብት ላይ ቀንሰን የምንገነባውን ግድብ ለመጠበቅ አረንጓዴ አሻራ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ስራ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለተጀመሩ ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ስራዎችም አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢንዱስትሪ የሚቀርቡ አብዛኛው ግብአቶች ከሚተከሉ ችግኞችና ከግብርና ምርቶች የሚገኙ መሆናቸውን አንስተዋል።
የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ለሚሰሩ የከተማ ልማት ስራዎች በስፋት ችግኝ መትከልና አካባቢን ማስዋብ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ውጤት በትጋት በመስራት ነው የሚጨበጠው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ በተከልን መጠን በሁሉም ዘርፍ የምናገኘው ውጤት እየጨመረ የኢትዮጵያም ውበት በጉልህ እየታየ ይሄዳል ብለዋል።
ያማረች፣ ንጹህ፣ ለኑሮ የምትመችና ለቱሪስት መስህብ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባትና ለማየት የሚፈልግ ትውልድ ቀላሉ ስራ ችግኝ መትከል መሆኑን ሊረዳ ይገባል ብለዋል።
ብዙ የልማት ስራዎች የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረንጓዴ አሻራ ግን በቀላሉ ልናሳካ የምንችለው በእጃችን ያለ ስራ ነው ብለዋል።
ችግኝ መትከል ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ኢንቨስትመንት መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም ሀገሩን የሚወድ ማንም ዜጋ ኢትዮጵያ የሰጠችውን መልሶ የሚከፍላት ችግኝ በመትከል ጭምር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አረንጓዴ አሻራ የመላ ኢትዮጵያውያን የመትከል፣ የመጠበቅና የማጽናት ስራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።