ቀጥታ፡

ኅብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን በማጠናከር የማይተካ ሕይወት ለመታደግ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ አለበት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ኅብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን በማጠናከር የማይተካ ሕይወት ለመታደግ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ እንዳለበት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ። 

20ኛው የዓለም ደም ለጋሾች ቀን ከሰኔ 7 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ሲካሄድ ቆይቷል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ ለደም ለጋሾች የምስጋናና ዕውቅና መርኃ ግብር ተካሂዷል።  

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ጊዜ፤ በርካታ ወገኖች በደም እጦት ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች እንደሚጋለጡ ጠቁመዋል። 

ዜጎችም ይህንን ከግምት በማስገባት ደም በመለገስ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው ይህም ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በተለይም ኅብረተሰበ ደም የመለገስ ባህሉን በማጠናከር ሕይወትን ለመታደግ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ባለፉት 11 ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ300 ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልጿል።

የዓለም ደም ለጋሾች ቀን ሁለንተናዊ ደኅንነቱ የተጠበቀ የደም ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው  ጥረት ትኩረት እንዲሰጥ ዓላማም ያነገበ ነው። 

በዛሬው መርኃ ግብር የጤና ሚኒስትርና የባለድርሻ አካላት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች  ጥር የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም