ቀጥታ፡

በአገሪቱ የማህበረሰቡን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያሳድጉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ

ሆሳዕና ፤ ሰኔ 22/2016 (ኢዜአ) ፡- በአገሪቱ የተለያዩ  የሃይል  አማራጮችን በመጠቀም የማህበረሰብን የኤሌክትሪክ  አገልግሎት  ተደራሽነትን የሚያሳድጉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር  ገለጸ።   

ሚኒስቴሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ግቤ ወረዳ በገሳዳና ኮደዳ ቀበሌ  በ25 ሚሊዮን ብር በጀት ያስገነባው  አነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዛሬ  ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።


 

ፕሮጀክቱን መርቀው አገልግሎቱን ያስጀመሩት  በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር  የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የተለያዩ የሃይል አማራጮች በመጠቀም የማህበረሰብን የሀይል ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በዚህም በተለይም ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር የኃይል አቅርቦት ማግኘት የማይችለውን የገጠሩን ማህበረሰብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።  

አሁን ላይ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኘውን የውሃ አማራጭ በመጠቀም 5 ሺህ አነስተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች  ግንባታ በመከናወን ላይ  እንደሚገኝ አስታውቀዋል ።  

ፕሮጀክቱ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፈ አነስተኛ ኃይል በሚፈልጉ የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።  

ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ ተመርቆ  ለአገልግሎት የበቃው አነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን እስከ 300 አባዎራዎችን የሀይል ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።  

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሌ በበኩላቸው ፤ የአሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማህበረሰቡ ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።  

ይህም በየአካባቢ የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በአነስተኛ ወጪ በመገንባት እንደሆነ ገልጸዋል።  

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር  በሰጠው ትኩረት በሀዲያ ዞን በለመሬ ወንዝ ላይ የተገነባው አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በክልሉ የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም አነስተኛ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ተሞክሮ የተወሰደበት ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።  

በግቤ ወረዳ ገሳደና ኮደዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሪት ሰናይት አሞሴ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም የእህል ወፍጮ ለማግኘት ረዥም ርቀት ለመጓዝ አልያም  በባህላዊ ወፍጮ ለመጠቀም ይገደዱ እንደነበር  ተናግራለች  ።  

ይህም ጊዜና ጉልበትን በማባክን ለእንግልት ሲዳርጋቸው እንደቆየ አውስተው፤ ዛሬ የተመረቀው ፕሮጀክት ችግሩን እንደሚያቃልላቸው ገልጸዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም