ቀጥታ፡

 የውሃ አካላትን ከብክለት ለመከላከል እምቦጭና lአረሞችን የማስወገድ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ የውሃ አካላትን ከብክለት ለመከላከል እምቦጭና ሌሎች አረሞችን በማስወገድ ብዝሃ ህይወትን የመጠበቅና ሃይቆችን ከደለል የመከላከል ተግባር ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።

የፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከሲዳማ ክልል ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከአባያ ሃይቅ ላይ የእምቦጭ አረምን የማስወገድ ስራ አከናውኗል፡፡

በዚሁ ወቅት በባለስልጣኑ ውሃና ውሃ ነክ መሬቶች ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ድረስ እንዳሉት፤ "ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው ሃገር አቀፍ ንቅናቄ ሶስተኛ ወሩን ይዟል።


 

የውሃ አካላትን ለብክለት የሚዳርጉ እምቦጭንና አረሞችን በማስወገድ ብዝሃ ህይወትን የመጠበቅና ሃይቆችን ከደለል የመከላከል ስራ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በአባያ ሐይቅና እምቦጭ አረም በተከሰተባቸው ሌሎች ሃይቆች ላይ አረሙን የማስወገድ ስራ በዘላቂነት ለመስራት  የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመዋል።

በሲዳማ ክልል ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ቲቦ በበኩላቸው፤ በክልሉ በተካሄደ ንቅናቄ የአየርና የውሃ ብክለትን በመከላከሉ ረገድ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

የአባያ ሃይቅ የዓሳ ምርት የሚገኝበትና ለወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ የእምቦጭ አረምን የመከላከል ስራ የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

የእምቦጭ አረምን በማስወገድ ስራ የተሳተፉ ወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ሃይቁን በባለቤትነት ሊጠብቁትና ሊንከባከቡ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በሲዳማ ክልል ሎካ አባያ ወረዳ በኩል ባለው የአባያ ሃይቅ ከ2 ሺህ 450 ሄክታር በላይ በእምቦጭ አረም መወረሩን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የብዝሃ ህይወት ዳይሬክተር አቶ ሃገሪሳ አማሮ ናቸው።


 

አረሙ በአባያ ሃይቅ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የአሳ ምርት የሚቀንስና በብዝሃ ሕይወት ላይ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ስራ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

በሎካ አባያ ወረዳ በማኅበር ተደራጅተው አሳ በማስገር ላይ የተሰማሩት አቶ ተካልኝ ጸሃይ፤ የእምቦጭ አረምን በማስወገዱ ዘመቻ ከተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።


 

አረሙ በሃይቁ ላይ መስፋፋቱን ተከትሎ የአሳ ምርቱ ከዚህ ቀደም የሚያገኙትን ያክል አለመሆኑን ጠቅሶ ፤ ላለፉት አራት ቀናት አረሙን የማስወገድ ዘመቻው ላይ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል። 

በሲዳማ ክልል ሎካ አባያ ወረዳ ከአባያ ሃይቅ ላይ እምቦጭ አረምን ለማስወገድ በተከናወነ የዘመቻ ስራ አሳ አስጋሪ ማህበራትን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች  ተሳትፈዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም