በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን ያገኘነውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እንሰራለን - ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን ያገኘነውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እንሰራለን - ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ቆይታ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፤ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖች አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው የፖሊስ መኮንኖች በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሌቭል አራትና በጤና ሳይንስ እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ወንጀልን መከላከልና በሳይንሳዊ መንገድ መመርመር የሚያስችል ጥልቅ እውቀት ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
በሚሰማሩበት የሙያ መስክ ዜጎችን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው በሰላምና ደኅንነት የትምህርት መስክ የተመረቀው ሳሙኤል አራጋው፤ ፖሊሳዊ ሙያ ከራስ በላይ ለሕዝብ ሰላምና ድኅንነት ቅድሚያ መስጠት በመሆኑ በቅንነትና በታማኝነት ሕዝቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራን በአግባቡ ለመወጣትም ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።
ኢንስፔክተር ማስተዋል ታዴ በበኩላቸው፤ በጥሩ ሥነ-ምግባር ሕብረተሰቡን እንደሚያገለግሉ ጠቅሰው፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው አስፈላጊ የሚባል እውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የፖሊስ ዋናው ተግባር በጀግንነት መጠበቅና በሰብዓዊነት ማገልገል ነው ያለው ሌላኛው ተመራቂ ጸጋነህ ፈለቀ፤ ሀገርን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑንም ጠቁሟል።
ተመራቂ ሳሙኤል አራጋው ለዜጎች መብት መከበር፣ ሰላምና ደኀንነታቸው እውን መሆንና ለፖሊሳዊ ሙያ ስኬት የበኩሉን ሚና ሊወጣ መዘጋጀቱንም ተናግሯል።
ኢንስፔክተር ማስተዋል ታዴ በበኩላቸው፤ ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ ወንጀልን በጋራ ከመከላከል አንጻር ሕብረተሰቡም የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ በመቀጠል ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል።
ኢንስፔክተር ድሪባ ቶሎሣ እንዳሉትም ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገት ጎዳና ከግብ እንዲደርስ በሙያቸው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ባገኘው የሕክምና ሙያ የሠራዊቱን አባላት እና የሕዝቡን ጤንነት ለመጠበቅ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የጤና ሳይንስ ምሩቁ ዘሪሁን ደጉ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የፖሊስ የሙያ መስኮች ከአጫጭር ኮርሶች እስከ ሁለተኛ ዲግሪ በማስተማር በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ብቁ የሆኑ የፖሊስ መኮንኖችንና ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የፖሊስ ሠራዊት ግንባታ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያኖረ ረዥም ዘመናትን የቆየ አንጋፋ ተቋም ነው።