ባለስልጣኑ በቡና ግብይት ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያንን የእርስ በእርስ ግንኙነት የምክክር መድረክ አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ በቡና ግብይት ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያንን የእርስ በእርስ ግንኙነት የምክክር መድረክ አካሄደ
ሀዋሳ ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ ቡና ከማምረት ባለፈ በቡና ግብይት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የአምራች፣ አቅራቢና ላኪ የግንኙነት መድረክ ማካሄዱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
ቡና አምራች ከሆኑ አራት ክልሎች የተውጣጡ የግብይት ተዋንያን በቡና ንግድ ዙሪያ የሚመክር መድረክ በሀዋሳ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንዳሉት በሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ምክንያት የቡና አምራች፣ አቅራቢና ላኪ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም።
“በቡና ንግድ ሂደት ውስጥ በርካታ ተዋንያን ያሉ ሲሆን በአምራች፣ አቅራቢና ላኪ መካከል ቀጥታ ግንኙነትና እርስ በእርስ ትውውቅ ባለመኖሩ ምክንያት ሌላ ሶስተኛ ወገን በመሀል በመግባት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ሲያገኝ ቆይቷል” ብለዋል።
ቡና ከ35 እስከ 40 በመቶ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የያዘ ከፍተኛ የስራ ዕድል የሚፈጠርበት ቢሆንም የአሰራር ስርዓት በአግባቡ ባለመዘርጋቱ ብዙ ጥቅም ማግኘት ሳይቻል መቆየቱን ገልጸዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት በቡና ግብይት ውስጥ የሚገኙ ተዋንያን ተገናኝተው እርስ በእርስ መምከር የሚችሉበትን መድረክ በመፍጠር ያሉትን ችግሮች መፍታት እንዲቻል መደረኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ውጪ የሚላከውን የቡና መጠን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ዶክተር አዱኛ ገልፀው ለውጥ በመምጣቱም በአሁኑ ወቅት በአመት ከ300 ሺህ ቶን ቡና በላይ መላክ መቻሉን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በክልሉ ከ168 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ማሳ አንደሚገኝና ሲዳማም በሀገሪቱ ከሚገኙ ቡና አምራቾች የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ክልሉ ከሚመረተው ቡና እስከ 30 ሺህ ቶን የሚደርስ ለውጪ ገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን የብዛት፣ የጥራትና የፋይናንሰ ችግሮችን ለመፍታት በአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን በቅንጅት ለመፍታት መሰል አውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከ300 የሚበልጡ ከሲዳማ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያና ከኦሮሚያ ክልሎች የተውጣጡ ቡና አምራች፣ አቅራቢና ላኪዎች ተሳታፊ ሆነውበታል።