ዩኒቨርሲቲው ለጎረቤት ሀገራት የሚሰጠው የትምህርት ዕድል ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም የምታበረክተው ጉልህ አስተዋጽኦ ማሳያ ነው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ለጎረቤት ሀገራት የሚሰጠው የትምህርት ዕድል ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም የምታበረክተው ጉልህ አስተዋጽኦ ማሳያ ነው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊስ ሠራዊቱን በእውቅትና ክህሎት ከማጎልበት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት እየሰጠ ያለው የትምህርት ዕድል ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም የምታበረክተው ጉልህ አስተዋጽኦ ማሳያ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖች አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው የፖሊስ መኮንኖች በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ድግሪ፣ በሌቭል አራት እና በጤና ሳይንስ እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው።
ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ፖሊሳዊ ሳይንስ፣ ስነ-ወንጀልና ወንጀል ፍትሕ እንዲሁም በፖሊስ መኮንንነት ዘርፍ አስፈላጊውን ሙያና እውቀት የጨበጡ መሆናቸው ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው ሰልጣኞች መካከል ሲያሰለጥናቸው የቆዩ 12 የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን የፖሊስ ሰልጣኞች ይገኙበታል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ፖሊስ ሰራዊት ህግ እንዲከበርና ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ትልቅ ሃላፊነት አለበት።
ተመራቂዎችም በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን እውቀትና ያላቸውን ልምድ በመጠቀም ህዝብን ያለ ልዩነት፣ እና በእኩልነት ማገልግል እንዳለባቸው ምልዕክት አስተላልፈዋል።
ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎችን በማከናወን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን የፖሊስ ሰራዊት አቅም በትምህርትና ስልጠና በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው በየጊዜው የስልጠና አድማሱን በማስፋት ለሰራዊቱ ተደራሽ ለማድረግ መስራት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ተወዳዳሪ የምርምርና የፖሊስ ትምህርት ተቋም ሆኖ ለመገኘት የበለጠ መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለጎረቤት ሀገራት የፖሊስ ሰራዊትና መኮንኖች የሚሰጠው የትምህርት ዕድል የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖራት ትስስር እንዲጠናከር ብሎም ሽብርተኝነትና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል እየተደረገ ላለው ትብብርና ቅንጅት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ፤ ዩኒቨርሲቲው የፌደራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ተቋማት፣ መንግስትና ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ በብቃት ለመወጣት እንዲችሉ ዘመኑ የሚፈልገውን የፖሊስ ክህሎትና እውቀት እያስጨበጠ ይገኛል፡፡
በዚህም ለሕገ-መንግስቱ መከበር በፅናት የሚታገልና ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት አክብሮ የሚያስከብር ከዘመኑ ጋር አብሮ የዘመነ የፖሊስ አባላትን፣ አመራሮችን የማፍራት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የፖሊስ የሙያ መስኮች ከአጫጭር ኮርሶች ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ በማስተማር ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካ ብቁ የሆኑ የፖሊስ መኮንኖችን እና ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በምረቃ መርሐ-ግብሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፣ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።